Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የትግራይ ሕዝብ ለሕገወጡ ቡድን መወገድ ያሳየው ቁርጠኝነት ከፍተኛ ፅናት የታየበት ነው – ከንቲባ ሺሻይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የትግራይ ሕዝብ ለሕገወጡ ቡድን መወገድ ያሳየው ቁርጠኝነት ከፍተኛ ፅናትና ጥንካሬ የታየበት ነው አሉ በትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር የመቐለ ከተማ ከንቲባ ሺሻይ አማረ(ዶ/ር)።

የመቐለ ከተማ ባለአደራ አስተዳደር ያለፉትን 30 ቀናት አፈጻጸም ገምግሟል።

ከንቲባ ሺሻይ (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ በከተማዋ የአገልግሎት ዘርፉን በፍጥነት ወደ ሥራ ለማስገባት የተሰጠው ትኩረት ቀናትን ብቻ እንዲፈጅ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

የተፈጠሩ የፀጥታ መዋቅሮች አሁን ላይ መቐለን ተኩስ የማይሰማባት ከተማ ወደ ማድረግ እየተሸጋገሩ እንደሚገኝም ጠቅሰው በከተማው ሰላምን ማረጋገጥ ቀዳሚ ትኩረት እንደተሰጠው ገልጸዋል።

በመቐለ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ለመከወን ሥራዎች መጀመራቸውን አንስተው በመቐለ የኮማንድ ፖስት ውሳኔን ተግባራዊ በማድረግ ማሕበረሰቡ ሰላሙን ማስጠበቅ እንዲችል እድል ተፈጥሯል ነው ያሉት።

የማሕበረሰቡን ሥነልቦና ወደ ሰላማዊ እና ፍትሃዊ እንቅስቃሴ ለመመለስ ባለፉት ሳምንታት የውይይት መድረኮች መመቻቸታቸውንም አስረድተዋል።

የሰብዓዊ ድጋፍን አስመልክቶ አግባብነቱን በተከተለ አካሄድ አቅርቦቱ እንዲጠናከር እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በመዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት በከተማዊ የሚስተዋሉ ሕገ ወጥ ተግባራትን የመከታተልና የማስቆም እንዲሆም የአገልግሎት ዘርፎችን ደህንነት መጠበቅ ትኩረት እንደተሰጠውም አስረድተዋል።

በአሸናፊ ሽብሩ

Exit mobile version