አዲስ አበባ፣ ሕዳር 14፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን ውጤታማ ለማድረግ በትኩረት እየሰራች ነው አሉ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ወ/ሮ ያስሚን ወሀብረቢ፡፡
የአፍሪካ ንግድ ልማት ፎረም “የአፍሪካን የወጪ ንግድ በጥራት መገንባት” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል፡፡
ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የተገበረቻቸው ቁልፍ የኢኮኖሚና የንግድ ማሻሻያዎች በግብርና፣ በማዕድንና በማኑፋክቸሪንግ ያለውን አቅም ለማውጣት እያገዙ ነው፡፡
በተጨማሪም ወደ ገበያ መር የውጭ ምንዛሪ ስርዓት የተደረገው ሽግግርና ለላኪዎች የሚሰጡ ማበረታቻዎች የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ፣ የወጪ ንግድንና ኢንቨስትመንትን በማሳደግ ላይ መሆናቸውንም ነው የገለጹት፡፡
በኢትዮጵያ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አሰጣጥን ዲጂታል ማድረግን ጨምሮ ግልጽ፣ አስተማማኝና ቀልጣፋ የንግድ አካባቢ ለመፍጠር ማሻሻያዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡
የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነት ከውስጥ ይጀምራል ያሉት ሚኒስትሯ፤ ደረጃዎችን ማውጣት፣ ምርመራ፣ ሰርቲፊኬሽንና እውቅና መስጠት የሚያከናውኑ ተቋማትን አቅፎ የያዘው የኢትዮጵያ የጥራት መንደር መገንባቱን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ሂደትን አጠናክራ መቀጠሏን ገልጸው፤ ይህም የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን በሕግና በደንብ ለማጠናከር፣ አስተማማኝ የዓለም ገበያ ተደራሽነትን ለማረጋገጥና የዓለም ንግድ ሕጎችን በመቅረጽ ለመሳተፍ ያግዛል ብለዋል።
ከታሪፍ ውጪ የሆኑ እንቅፋቶችን፣ ከፍተኛ የሎጂስቲክስና የንግድ ፋይናንስ ወጪዎችን ለመፍታት አፍሪካ በአንድ ድምፅ መቆምና በአንድ የአፍሪካ ሀገር ጥራቱ የተረጋገጠ ምርት በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተቀባይነት የሚያገኝበትን ስርዓት ማስፈን ይገባል ነው ያሉት፡፡
አፍሪካ ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት፣ ወጣትና ታታሪ ሕዝብ እንዲሁም እያደገ የመጣ ገበያ ቢኖራትም፤ በዓለም አቀፍ ንግድ ያላት ተሳትፎ አሁንም በጥሬ ዕቃዎችና በመሠረታዊ ምርቶች ላይ የተወሰነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይህንን ለመለወጥ ወደ እሴት ጭማሪና የኢንዱስትሪ ልማት እንዲሁም ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃዎችን የሚያሟሉ ምርቶችንና አገልግሎቶችን ወደ ማምረት መሸጋገር ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን ውጤታማ ለማድረግ በድንበር ተሻጋሪ የመንገድ፣ የባቡር፣ የኃይል ትስስርና የአንድ መስኮት ድንበር ጣቢያዎች ልማት ላይ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ፎረሙ ከውይይት ባሻገር ለተጨባጭ አጋርነትና ለጋራ ርምጃ መነሻ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል፡፡

