Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሴኔጋል የአፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮንነት ተረጋገጠ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 15፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ሴኔጋል በአፍሪካ ዋንጫ ያገኘችው የሻምፒዮንነት ውጤት በዓለም አቀፉ የስፖርት ገላጋይ ፍርድ ቤት በተሰጠ ውሳኔ ተረጋግጧል።

በውዝግብ የተጠናቀቀው የ2025 የአፍሪካ ዋንጫ ፍጻሜ ውጤት በዓለም አቀፉ የስፖርት ገላጋይ ፍርድ ቤት ውሳኔ የተቀየረ ሲሆን፣ ሴኔጋል የሻምፒዮንነት ስያሜን እንደገና ማግኘቷ ተገልጿል።

ሴኔጋል ከሞሮኮ ጋር ባደረገችው የአፍሪካ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ በተጨማሪ ሰዓት ባስቆጠረችው ግብ 1 ለ 0 ማሸነፏ ይታወሳል። ሆኖም በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ለሞሮኮ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ተከትሎ የሴኔጋል ተጫዋቾች ለተወሰነ ጊዜ ሜዳውን ለቀው መውጣታቸው አከራካሪ ሁኔታ ፈጥሮ ነበር።

ይህን ተከትሎም የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን የይግባኝ ቦርድ በሴኔጋል ተጫዋቾች ሜዳውን ለቀው መውጣት ምክንያት ቡድኑ ጨዋታውን በሕግ እንደተሸነፈ በመቁጠር ውጤቱን ወደ 3 ለ 0 በመቀየር አሸናፊነቱን ለሞሮኮ ሰጥቶ ነበር።

የሴኔጋል እግር ኳስ ፌዴሬሽን በውሳኔው ላይ ይግባኝ ካቀረበ በኋላ የዓለም አቀፉ የስፖርት ገላጋይ ፍርድ ቤት የዳኞች ቡድን ጉዳዩን መርምሮ የሴኔጋልን የሻምፒዮንነት ማዕረግ እንዲመለስ ወስኗል።

በዚህም የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን በፍጻሜው ሜዳ ላይ ያስመዘገበው ድል እንዲጸና በማድረግ የ2025ቱ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊነቱን በይፋ መልሶ ማግኘቱን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል።

በዮናስ ጌትነት

Exit mobile version