ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ባስመዘገበቻቸው ውጤቶች የአፍሪካን የመቻል አቅም እያሳየች ነው – ዶ/ር መቅደስ ዳባ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 16፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ባስመዘገበቻቸው ተጨባጭ ውጤቶች የአፍሪካን የመቻል አቅም በተግባር እያሳየች ነው አሉ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ።
ከ100 በላይ ሀገራት የተውጣጡ ከ30 ሺህ በላይ ታዳሚዎች እየተሳተፉበት የሚገኘው 5ኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ (CPHIA 2026) በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እየተካሄደ ነው።
የጤና ሚኒስትሯ እንደገለጹት፤ ከጤናው ዘርፍ ባሻገር የገንዘብ፣ የዕቅድ፣ የግብርና እና የአካባቢ ጥበቃ ዘርፎችን የወከሉ ከ46 በላይ ሚኒስትሮች በጉባኤው መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
የጉባኤው ታዳሚዎች የኢትዮጵያን ውጤታማ ተሞክሮ እና በሌሎችም ዘርፎች እየተመዘገቡ ያሉ ሁለንተናዊ ለውጦችን መመልከታቸውን አንስተው ይህም ሀገሪቱ ያላትን የመሥራትና የመፈጸም አቅም በተግባር በማሳየት በአህጉሪቱ ላይ እምነት እንዲጣል ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን አብራርተዋል።
ተቋማት፣ አጋሮችና የግል ድርጅቶች በጋራ እየተወያዩበት ባለው በዚህ መድረክ፤ ኢትዮጵያ በሳይንስ ዘርፍ ያከናወነቻቸውን ሥራዎች በተለያየ መንገድ እያቀረበች እንደምትገኝም ጠቁመዋል።
ተሳታፊዎችም ኢትዮጵያ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በዲጂታል ጤና፣ በመጀመሪያ ደረጃ ጤና እንክብካቤ እና በሕክምና ሪፈራል ሥርዓት የሠራቻቸውን ውጤታማ ሥራዎች መመልከታቸውንም አስረድተዋል።
በዚህም በርካታ ሀገራት የኢትዮጵያን ሞዴሎችና የዲጂታል አሠራሮች በሀገራቸው ለመተግበር ፍላጎት ማሳየታቸውንና የልምድ ልውውጥ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
የዓለም የጤና አስተዳደር ሥርዓት እየተቀየረ መሆኑን እና አፍሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽዕኖ ፈጣሪ እንድትሆን ኢትዮጵያ የጤና ዲፕሎማሲን በስፋት እየተጠቀመች ትገኛለችም ነው ያሉት።
ጉባኤው የአፍሪካን የጤና ሉዓላዊነት ወደ ተጨባጭ ውሳኔዎች የሚያሸጋግር መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ አፍሪካ በዓለም አቀፍ የጤና ውይይቶችና በሳይንስ ትግበራዎች ተቀባይ ብቻ ሳትሆን ሰጪም ሆና እየወጣች ነው ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

