አዲስ አበባ፣ ሕዳር 15፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ለሀገር ውስጥ የመድኃኒት ምርት በሰጠችው ልዩ ትኩረት ለዓመታት ከ8 እስከ 10 በመቶ የነበረውን የሀገር ውስጥ አምራቾች ድርሻ ወደ ከ44 በመቶ ማድረስ ችላለች፤ በ2030 ከ50 በመቶ በላይ ለማድረስ እየተሰራ ነው።
በመድኃኒት ምርት ራስን መቻል ለኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ልማት አጀንዳ ብቻ ሳይሆን፣ የብሔራዊ ጤና ደህንነት፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት እና ፍትሐዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳካት ዋነኛ ምሰሶ ነው።
ኢትዮጵያም ለዓመታት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ሲገዙ የነበሩ መሠረታዊ መድኃኒቶችን እና የሕክምና ግብዓቶችን በራስ አቅም ለማምረት የፖሊሲ ማሻሻያዎችን እና የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎችን ተግባራዊ አድርጋ ወሳኝ ስኬት እያስመዘገበች ትገኛለች፡፡
መንግሥት የሀገር ውስጥ ምርትን ለማበረታታት እስከ 25 በመቶ የዋጋ ልዩነት ማበረታቻን ጨምሮ የቅድሚያ ግዥ መብት ፣ የታክስና የጉምሩክ እፎይታ እንዲሁም እንደ ቂሊንጦ የመድኃኒት ኢንዱስትሪ ፓርክ ያሉ ልዩ የማምረቻ ማዕከላትን የማዘጋጀት ተግባራትን እያከናወነ ነው።
በኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት እና በጤና ሚኒስቴር መረጃ መሠረት፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሀገር ውስጥ አምራቾች የመንግሥትን ዓመታዊ የመድኃኒት ፍላጎት የመሸፈን ድርሻ ከነበረበት ዝቅተኛ ደረጃ ወደ 44 በመቶ አካባቢ ከፍ እንዲል አስችሏል።
በተጓዳኝም፣ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን የቁጥጥር ሥርዓቱን በማዘመንና ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃዎችን (GMP) በማስፈን፣ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ መድኃኒቶች ደህንነታቸው የተጠበቀና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራዎችም እየተተገበሩ ነው።
ኢትዮጵያ የተጀመረውን የመድኃኒት ምርት ሽግግር ዘላቂ ለማድረግ ያለቀላቸው መድኃኒቶችን ከማምረት ባለፈ የሀገር ውስጥ የጥሬ ዕቃ አቅርቦትን ማሳደግ፣ በምርምርና ልማት ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ እንዲሁም የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ትብብርን ማጠናከር ሥራዎችን አጠናክራ ማስቀጠል ይጠበቅባታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ5ኛው የአፍሪካ ዓለም አቀፍ የህበረተሰብ ጤና ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ኢትዮጵያ ባላት የሰው ኃይል፣ በሀገር ውስጥ የመድኃኒት ምርት፣ በዲጂታል ጤና እና በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ላይ ኢንቨስት በማድረግ የማይበገር እና ራሱን የቻለ የአፍሪካ የጤና ሥርዓት ለመገንባት ቁርጠኛ ናት ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ መድኃኒቶችን እና የህክምና ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ በራስ አቅም በማምረት ለአፍሪካ የጤና ሥርዓት ምሳሌ የሚሆኑ ሥራዎች እያካሄደች ሲሆን ይህ በአህጉሪቱ እውን እንዲሆን በቁርጠኝነት እንደምታግዝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ገልጸዋል፡፡
የውጭ ጥገኝነት መቀነስ በጤና ተቋማት የሚታየውን የመድኃኒት እጥረት ያቃልላል፡፡ ለባለሙያዎች የሥራ ዕድል እና የዕውቀት ሽግግር ይፈጥራል፡፡ ወረርሽኞችን እና ድንገተኛ የጤና ሥጋቶችን በራስ አቅም የመመከት ብቃትንም ያሳድጋል።
ይህን ዕውን በማድረግ በገጠርም ሆነ በከተማ ለሚገኝ እያንዳንዱ ዜጋ ጥራት ያለውና ተመጣጣኝ ዋጋ ያለው መድኃኒት በአስተማማኝ ሁኔታ በማቅረብ ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ያስችላል፡፡

