Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የክትፎ ዲፕሎማሲ፡ ከኢትዮጵያ ማዕድ እስከ ዓለም አቀፍ መድረክ የሚዘልቀው ገር ኃይል

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 16፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በዘመናዊው የዓለም አቀፍ ግንኙነት መድረክ ሀገራት ተጽዕኗቸውን የሚያሳርፉት በፖለቲካዊ ድርድር ወይም በኢኮኖሚያዊ አቅም ብቻ አይደለም።

ዛሬ ዛሬ “የማዕድ ዲፕሎማሲ” (Culinary Diplomacy) የአንድን ሀገር ባህል፣ ታሪክና ማንነት ለዓለም ለማስተዋወቅ እንደ ዋነኛ ገር ኃይል እያገለገለ ይገኛል።

ለዚህም የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግቦች፣ በተለይም የክትፎ ዝና በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ዘንድ እያገኘ ያለው ትኩረት ህያው ምስክር ነው።ይህንን እውነታ ታዋቂው የዓለም አቀፍ የዜና አውታር ሲኤንኤን (CNN) “የኢትዮጵያ ምግቦች፡ 15ቱ ምርጥ ጣዕሞች” በሚል ባወጣው ሰፊ ዘገባ አጠናክሮታል።

ዘገባው የኢትዮጵያን ማዕድ ከተቀረው አፍሪካ ልዩ እና ማራኪ በሆነ ባህላዊ ቅርስ የተገነባ፣ እንዲሁም የዓለም “በሚስጥር የተያዘ ድንቅ ሀብት” ሲል ያሞካሸዋል።

በዚህ የዓለም አቀፍ አድናቆት ዝርዝር ውስጥ ክትፎ ከቀዳሚዎቹ ተርታ መሰለፉ፣ ምግቡ ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ያለውን ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት ያሳያል።

ሲኤንኤን ክትፎን ለዓለም አንባቢያን ሲያስተዋውቅ፣ ከፈረንሳዮች ታዋቂ ምግብ ጋር በማነጻጸር የራሱ የሆነ ልዩ ኢትዮጵያዊ ለዛ እንዳለው ይገልጻል።

ከምርጥ ቀይ ስጋ ተከትፎ፣ በቅቤና በሚጥሚጣ ታሽቶ፣ በአይብና በጎመን ታጅቦ የሚቀርበው ክትፎ—ጥሬም ሆነ ለብ ለብ—የኢትዮጵያውያን የክብር እንግዳ መቀበያና የደስታ መግለጫ ነው።

ዘገባው የምግቡን በንጥረ ነገሮች የበለጸገ መሆኑን እና እና ከአድካሚ የአሰራር ሂደት በኋላ የሚሰጠውን ልዩ እርካታ በአድናቆት ማስፈሩ፣ የኢትዮጵያን የምግብ ጥበብ ጥልቀት ለዓለም የሚመሰክር ነው።

ይህ የክትፎ እና መሰል የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግቦች ዓለም አቀፋዊ ተወዳጅነት፣ ለሀገራችን የሚያስገኘው ፋይዳ ከማዕድ ጣዕም እጅግ የላቀ ነው።

በመጀመሪያ ደረጃ፣ እንደ ሲኤንኤን ያሉ ግዙፍ የሚዲያ ተቋማት የኢትዮጵያን ባህላዊ ምግቦች ሲያወድሱ፣ የሀገሪቱን የረጅም ዘመን ስልጣኔና የእንግዳ ተቀባይነት እሴት በቀጥታ ለሚሊዮኖች በማስተዋወቅ ጠንካራ የገጽታ ግንባታ ይሰራሉ።

ይህ የሚዲያ ትኩረት በምላሹ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ዋና ዋና ከተሞች ያሉ የኢትዮጵያ ምግብ ቤቶችን ወደ “ባህላዊ ኤምባሲነት” ይቀይራቸዋል፤ ክትፎን የቀመሰ የውጭ ዜጋም የምግቡን መነሻ ሀገር ለመጎብኘት መጓጓቱ የቱሪዝም ዘርፉን ያነቃቃል።

ከዚህም ባሻገር፣ ከአንድ ገበታ ላይ በጋራ የመመገብና የመጎራረስ ባህላችን፣ ለዓለም የሰላምና የአብሮነት መልዕክትን የሚያስተላልፍ ድንቅ ዲፕሎማሲያዊ እሴት ሆኖ ያገለግላል።

በአጠቃላይ፣ ክትፎ ከምግብነት ባለፈ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሀብት፣ ታሪክና እንግዳ ተቀባይነት ለዓለም የሚያስተዋውቅ ድምጽ አልባ አምባሳደር ነው።

ይህንን ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች “በሚስጥር የተያዘ ድንቅ ሀብት” ያሉትን ባህላዊ እሴት በዘመናዊ አቀራረብና በተቀናጀ የሚዲያ ሽፋን ይበልጥ በማስተዋወቅ፣ የክትፎ ዲፕሎማሲን ለሀገራችን ሁለንተናዊ እድገትና ገጽታ ግንባታ ልንጠቀምበት ይገባል።

በኃይለየሱስ መኮንን

Exit mobile version