አዲስ አበባ፣ ሕዳር 16፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ እና የሱዳን ህዝቦች በባህል፣ በታሪክ፣ በኢኮኖሚ፣ በንግድ እና ወንድማማችነት ላይ የተመሠረተ ጠንካራ ትስስር አላቸው፡፡ የሀገራቱ ሰላም እና ልማት በእጅጉ የተሳሰሩ እና የማይነጣጠሉ ናቸው፡፡
ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሱዳን ሰላም ከኢትዮጵያ ሰላም የማይነጠል እና ለአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት ወሳኝ ምሰሶ መሆናቸውን በአፅንኦት የገለጹት። በዚህ ምክንያትም ኢትዮጵያ ለሱዳን ህዝብና መንግሥት ሰላምና መረጋጋት በግንባር ቀደም ተሳታፊነት ትታወቃለች፡፡
በሱዳን ውስጣዊ አለመረጋጋትና ግጭት ሲፈጠር ሰላም የማስፍንና የማረጋጋት ሥራዎችን በመስራት እንዲሁም የተለያዩ የሀገሪቱ የፖለቲካ እና ወታደራዊ ቡድኖች በጠረጴዛ ዙሪያ ልዩነቶቻቸውን በውይይት በመፍታት ሰላም እንዲያወርዱ ተደጋጋሚ ጥረት አድርጋለች፣ አሁንም እያደረገች ነው፡፡
በዚህ ረገድ በዳርፉር በተካሄደው የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት የጋራ ኦፕሬሽን ውስጥ በመሳተፍ፣ የሲቪል ህዝብ ጥበቃንና የሰብዓዊ እርዳታ ጥረቶችን ለመደገፍ ወታደሮችን፣ ታዛቢዎችን እንዲሁም ሌሎች ቴክኒካል ድጋፎችን በማበርከት ለሱዳን ሰላም መስፈን ተግታለች።
እንዲሁም ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን አከራካሪ የሆነውን የአቢዬይ ክልል ለማረጋጋትና ሰላም ለማስፈን የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ተሰማርቶ በአካባቢው የሲቪሎችን ደህንነት በመጠበቅ እና በድንበር አካባቢ ሰላም እንዲሰፍን በማድረግ ተልዕኮውን ተወጥቷል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በ2011 ዓ.ም ከሱዳኑ ታኅሣሥ አብዮት በኋላ በሲቪሉና በወታደራዊው ቡድኖች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት በስምምነት እዲፈታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ካርቱም ተጉዘው ለማስማማት ጥረት አድርገዋል፡፡ ይህ ኢትዮጵያ በሱዳን ሰላም እንዲሰፍንና ያላትን ቁርጠኝነት የሚያመላክት ነው፡፡
አሁን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የሱዳን ተፋላሚ ወገኖች ችግሮቻቸውን በምክክርና ውይይት በመፍታት ሰላም እንዲያወርዱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዐረብኛ ቋንቋ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊ እና የሲቪል ቡድኖችን ጨምሮ ሁሉም የሱዳን ወገኖች ምክክር የሚያደርጉበት “ሱዳን ለሱዳን” የተሰኘ መድረክ ኢትዮጵያ ማዘጋጀቷን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት እና አመቻችነት በሚካሄደው በዚህ የምክክር ጥሪ ሁሉም የሱዳን ወገኖች እንዲሳተፉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠይቀዋል።
የ”ሱዳን ለሱዳን” ምክክሩ ዋና ዓላማ ጦርነቱን እና መከፋፈልን በማቆም ለዘላቂ ሰላም መሠረት የሚሆን ብሔራዊ ስምምነት ላይ መድረስ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በመልዕክታቸው ጠቅሰዋል።
በኃይል የሚጫኑ የመፍትሔ ሃሳቦች ለሱዳን ዘላቂ ሰላም እንደማያመጡ ጠቅሰው፤ የሱዳን መጻኢ ዕድል በሱዳን እና በሱዳናዊያን ብቻ መወሰን እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በሱዳን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ የሚመራው የሲቪሎች ጥምረት የሆነው የሲቪል ዴሞክራሲያዊ ህብረት አብዮታዊ ኃይል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ያቀረቡትን የሰላም ሀሳብ የሚቀበለው መሆኑን አረጋግጧል። የሰላም ሀሳቡ በሱዳን ያለውን ግጭት ለመፍታት አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጿል።
በተመሳሳይ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል የቀረበውን የሰላም ሀሳብ በመቀበል ለሀገሪቱ ሰላም ለመስራት ዝግጁ እንደሆነ አመልክቷል።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የኮሙኒኬሽን ኃላፊ ካሊድ አህመድ ዳና ለሬዲዮ ታማዙጅ እንደገለጹት፤ የቀረበው የሰላም ሀሳብ በሱዳን ያለውን ጦርነት ከማስቆም ባሻገር የሱዳን ህዝብ በጦርነቱ ምክንያት ከገባበት መከራ እንዲወጣ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
ሱዳን ከገባችበት ቀውስ እንድትወጣ፣ አንድነቷ እና ሉዓላዊነቷ እንዲጠበቅ የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህዝብ ያሳዩትን አጋርነት አድንቀዋል።
ሰላም የማስከበር ለሰላም የመቆም ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ፤ ይህንን ሚናዋን በጎረቤት ሱዳንም ሳታሰልስ እየተወጣች ትገኛለች፡፡
በቴዎድሮስ ሳህለ

