አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የሳሳካዋ አፍሪካ አሶሴሽን 40ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ሲምፖዚየም ከሕዳር 22 እስከ 23 ቀን 2019 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
“የአፍሪካን የምግብና የሥርዓተ ምግብ ዋስትና እንደገና ማሰብ” በሚል መሪ ሐሳብ የሚካሄደው የሁለት ቀናት ሲምፖዚየም ከፍተኛ የግብርና ልማት መሪዎችን፣ የውሳኔ ሰጪ አካላትን፣ አርሶ አደሮችን፣ ተመራማሪዎችን፣ የልማት አጋሮችንና የግሉ ዘርፍ ተወካዮችን ያሳትፋል።
የሲምፖዚየሙ ዋና ዓላማ ባለፉት አራት አስርት ዓመታት በአፍሪካ የግብርና ሽግግር የተመዘገቡ ለውጦችን መገምገም፣ የወደፊቱን የግብርናና የምግብ ሥርዓት አቅጣጫ መመልከት፣ እንዲሁም በዘርፉ ያሉ ባለድርሻ አካላት መካከል ውይይትና አዳዲስ አጋርነቶችን ማበረታታት መሆኑ ተገልጿል።
የዝግጅቱ መርሐ ግብር ከፍተኛ ደረጃ ያላቸውን የፖሊሲ ውይይቶች ከተግባራዊ የልምድ ልውውጦች ጋር በማጣመር በግብርና ኤክስቴንሽ፣ በአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን መቋቋም፣ በምግብና በሥርዓተ ምግብ ዋስትና፣ በኢንቨስትመንትና ፈጠራ እንዲሁም አካታች የእሴት ሰንሰለት ልማት ላይ ያተኮሩ ውይይቶችን ያካትታል።
ሲምፖዚየሙን የናይጄሪያ የቀድሞ ፕሬዚዳንትና የሳሳካዋ አፍሪካ አሶሴሽን የቀድሞ የቦርድ አባል ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ እንደሚመሩት ተጠቁሟል።
ዋና መሥሪያ ቤቱን በጃፓን ቶኪዮ ያደረገው እና በፈረንጆቹ 1986 የተመሠረተው ሳሳካዋ አፍሪካ አሶሴሽን ከአርሶ አደሮችና ከተለያዩ አጋሮች ጋር በመሥራት በአፍሪካ ዘላቂ የግብርና ሽግግርን፣ የምግብና የሥርዓተ ምግብ ዋስትናን እንዲሁም አካታች የግብርናና የምግብ ሥርዓትን ለማጠናከር እየሠራ ይገኛል።
ይህ ዓለም አቀፍ ተቋም በ17 የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ባከናወናውቸ ሥራዎች የግብርና ኤክስቴንሽን ሥርዓቶችን አጠናክሯል፣ የተሻሻሉ የግብርና አሠራሮችን አስፋፍቷል፣ እንዲሁም አርሶ አደሮችንና ሌሎች የእሴት ሰንሰለት ተዋናዮችን፣ ከእውቀት፣ ቴክኖሎጂ እና ገበያ ጋር ማስተሳሰር ችሏል።

