Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የደም አቅርቦት እጥረት ለመቅረፍ ያለመው ዘመቻ “ዘ ሂውማን ቼይን”

አዲሱን ትውልድ በበጎ ፈቃደኝነት ደም እንዲለግስ ለማነሳሳትና በሀገሪቱ የሚታየውን የደም አቅርቦት እጥረት ለመቅረፍ ያለመ “ዘ ሂውማን ቼይን” የተሰኘ ሀገር አቀፍ ዘመቻ ዛሬ ይፋ አደረገ።

ዘመቻውን የኢትዮጵያ ደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎት ከዓለም አቀፉ የጤና ተቋም አቦት ጋር በመተባበር ነው ያዘጋጁት።

ዘመቻው በዋናነት ወጣቶችን በማንቀሳቀስ፣ ስለ ደም ልገሳ ያሉ የተሳሳቱ አመለካከቶችን በማስወገድና ቋሚ የበጎ ፈቃድ ለጋሾችን በማፍራት አሳሳቢውን የደም እጥረት ለመፍታት ያለመ ነው።

አንዲት ሀገር መሠረታዊ የደም ፍላጎቷን ለማሟላት ቢያንስ 1 በመቶ የሚሆነው ሕዝቧ (ከ1,000 ሰዎች 10 ሰዎች) ደም መለገስ እንደሚኖርባት የዓለም ጤና ድርጅት መስፈርት ያመላክታል፡፡

በዚህ ስሌት መሠረት ኢትዮጵያ በዓመት 1.1 ሚሊዮን ዩኒት ደም የሚያስፈልጋት ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት እየተሰበሰበ ያለው ወደ 476,000 ዩኒት ገደማ ብቻ ነው። ይህም የዓለም ጤና ድርጅት ያስቀመጠውን ዝቅተኛ መስፈርት 43.1 በመቶ ብቻ የሚያሟላ መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አሸናፊ ታዘበው፣ አሁን ላይ በሀገሪቱ የሚሰበሰበው ደም 99 በመቶው በበጎ ፈቃደኞች የሚገኝ መሆኑን እንደ መልካም እርምጃ ጠቅሰዋል።

ሆኖም አሁንም ከዝቅተኛው መስፈርት ግማሽ ያህሉን ብቻ እየተሰበሰበ መሆኑን አንስተው፤ «መስፈርቱን የሚያሟላ እያንዳንዱ ወጣት በዓመት ሦስት ጊዜ ደም ቢለግስ ይህን ክፍተት በእጅጉ መሙላት እንችላለን» ብለዋል።


በዘመቻው ማስጀመሪያ መርሐ ግብር መሠረት የመጀመሪያው የደም ልገሳ ሥነ-ሥርዓት ዛሬ ቅዳሜ ኅዳር 19 ቀን 2019 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ዋና መሥሪያ ቤት ፊት ለፊት በሚገኘው የመነሻ ምድር ሐውልት አካባቢ ተካሂዷል።

መርሐ ግብሩ በቀጣዮቹ ሦስት ወራት ውስጥ በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ የወጣቶች ማኅበራትና የተለያዩ ማኅበረሰቦች ዘንድ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

ወጣቶችን ለመጀመሪያ ጊዜ ደም እንዲለግሱና ቋሚ ለጋሽ እንዲሆኑ የማንቃት ሥራ እንደሚከናወን ነው የተገለጸው፡፡

 

Exit mobile version