Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ቀይ ባህርና ዓባይ፤ የኢትዮጵያ የህልውና እና የዲፕሎማሲ ምህዳር

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ዓባይ ከኢትዮጵያ ተራሮች ተነስቶ ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የልማትና የትብብር ምንጭ እንደሚሆን ሁሉ፣ ቀይ ባህርም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ከዓለም ገበያ ጋር የሚያስተሳስር ታሪካዊ መስመር ነው።

የቀይ ባህርና የባህር በር ጉዳይ በኢትዮጵያ የህልውና፣ የደህንነት፣ የልማትና የዲፕሎማሲ ስሌት ውስጥ የሚቀመጥ ዘመን ተሻጋሪ አጀንዳ ነው።

ከአፍሪካ ቀንድ በቆዳ ስፋቷ፣ ከአንድ መቶ ሰላሳ ሚሊየን በላይ በሚሆን የሕዝብ ብዛቷ፣ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴዋና በዲፕሎማሲያዊ ማዕከልነቷ ወሳኝ ስፍራ ያላት ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ጋር ያላት ቁርኝት በታሪክ፣ በጂኦግራፊ፣ በኢኮኖሚና በብሔራዊ ደህንነት የተሳሰረ የህልውና ጉዳይ ነው።

የባህር በር መዳረሻ ማግኘት ስትራቴጂካዊ ቁሳቁሶችን ያለ ውጭ ጫና በቀጥታ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ እና እንዲወጡ ከማስቻል ባሻገር ኢትዮጵያ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በዲፕሎማሲ ተጽዕኖ ለማሳደር የምትፈልገውን አቅም የሚያጎለብት መሠረት ነው።

የቀይ ባህር፣ የባቤል መንደብ ወሽመጥ እንዲሁም የአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ለአካባቢው ብቻ ሳይሆን ለአህጉሩና ለዓለም ትልቅ ስትራቴጂካዊ ፋይዳ አላቸው። በዚህ አካባቢ የሚከሰት ማንኛውም የፖለቲካና የጸጥታ መናወጥ በቀጥታ በኢትዮጵያ ህልውና ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል።

በሌላ በኩል የቀይ ባህር ቀጣና በአሁኑ ወቅት የዓለም ኃያላን ሀገራት ፍላጎት የሚጋጭበትና ተለዋዋጭ የጸጥታ ሁኔታ የሚታይበት ስፍራ ሆኗል። ሕገወጥ የሰዎችና የጦር መሣሪያ ዝውውር፣ የባህር ላይ ውንብድናና የሽብርተኝነት ስጋቶች ያለ ቀጠናዊ ትብብር የሚመከቱ አይደሉም።

ኢትዮጵያ በቀጠናው የባህር ጠረፎች ላይ ያላትን ንቁ ተሳትፎ ማሳደግና አስተማማኝ የባህር ኃይሏን ማጠናከሯ የንግድ መርከቦችንና የዓለም አቀፍ የንግድ መስመሮችን ደህንነት በማስጠበቅ፣ እንዲሁም ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ በመከላከል በቀጣናው ወሳኝ ሚና እንድትጫወት ያስችላታል።

ይሁን እንጂ በአካባቢው ኃያል ሆኖ የሚወጣ ሀገር ሲኖር ‘ቦታዬ ይነጠቃል’ ከሚሉ አመለካከቶችና ሌሎች ምክንያቶች የተነሳ የባህር በር ጥያቄ ያለ ፈተና የሚፈታ ጉዳይ አይደለም።

እነዚህን እንቅፋቶች በጋራ በመሥራትና የጋራ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ለመቅረፍ ኢትዮጵያ እየተከተለች የምትገኘው ሰላማዊ አካሄድ የሚደነቅ ነው።

ኢትዮጵያ በምታከናውነው ሰላማዊ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት፣ በርካታ የዓለም ኃያላን ሀገራት ጭምር ኢትዮጵያ በቀይ ባህር፣ በባቤል መንደብና በአፍሪካ ቀንድ የጸጥታ ጉዳዮች በንቃት የመሳተፍ ሕጋዊ መብቷን እየደገፉ ይገኛሉ።

በተለይም ኢትዮጵያ የምታነሳው የባህር በር ጥያቄ የልማትና የደህንነት ጉዳይ በመሆኑ፣ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሀገራት ሁሉ ጋር በሚደረግ ውይይት፣ ድርድርና ስምምነት እንዲፈታ ድጋፋቸውን በመስጠት ላይ ናቸው።

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የታሪክ፣ የኢኮኖሚና የደህንነት ጉዳይ ሆኖ፣ ምላሽ ማግኘቱ መላውን የአፍሪካ ቀንድ በዘላቂ ሰላም፣ በንግድ፣ በሎጂስቲክስ፣ በኃይል ትስስርና በልማት ለማስተሳሰር ወሳኝ እርምጃ ነው።

በመሆኑም ጉዳዩን በሰላማዊ ዲፕሎማሲ፣ በውይይትና በድርድር በመፍታት፣ ከግጭትና ከመናቆር ባሻገር ለቀጣዩ ትውልድ የጋራ ልማትና ደህንነት ማውረስ የሚቻልበትን አቅጣጫ በጋራ መከተል የወቅቱ ጥሪ ነው።

በዮናስ ጌትነት

Exit mobile version