አዲስ አበባ፣ ሕዳር 20፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀገር መከላከያ ሰራዊት የቴክኖሎጂ፣ የሰው ኃይል፣ የሎጂስቲክስና የአሠራር አቅም ማደግ በዘመናዊው ዓለም ለሀገራዊ ደህንነትና ህልውና መሠረት ነው፡፡
የ91 ዓመት እድሜ ባለጸጋው የኢትዮጵያ አየር ኃይልም በታሪካዊ ተልዕኮን አፈጻጸም ብቃቱ ላይ ተቋማዊ ለውጥ አክሎበት ከጅምሩ እስከ ዛሬ በዘለቀ ብቃት ላይ ይገኛል፡፡
የሀገርን የአየር ክልል ደህንነት ለመጠበቅ የተመሠረተው ተቋሙ፤ በተለያዩ የታሪክ ወቅቶች እየተለዋወጡ የሚመጡ የደህንነት ሁኔታዎችን ለመቋቋም አቅሙንና አደረጃጀቱን እያሳደገ መጥቷል።
በተቋሙ የረጅም ዓመታት የሥራ ልምድ ላይ ተመሥርቶ የተጀመረው የዘመናዊነት ጉዞ በተለይ በቴክኖሎጂ ማሻሻል፣ በሰው ኃይል ልማት፣ በሥልጠና፣ በጥገና እና በምርት አቅም ግንባታ ላይ ያተኮረ ነው።
አየር ኃይሉ በቅርቡ ከሩሲያ 12 የ4ኛ ትውልድ ፕላስ ፕላስ ሱ-35 ተዋጊ ጄቶችን የተረከበ ሲሆን፤ ይህም ተቋሙን የአየር የበላይነትና ዘመናዊ የውጊያ አቅምን ከሚያጠናክሩ ዋነኛ ርምጃዎች አንዱ ነው።
ሱ-30 ኬ ተዋጊ ጄቶችና ያክ-130 የሥልጠናና የውጊያ አውሮፕላኖችም የአየር ኃይሉን አቅም ወደ አዲስ ከፍታ ያሳድጉታል።
ተቋሙ የሀገሪቱን የአየር ክልል በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ የሚያስችሉ አራት የኤስ-400 የአየር መከላከያዎችን መታጠቁም የዚሁ ጥረት አካል ነው፡፡
በተጨማሪም በአየር ላይ ነዳጅ መሙላት የሚችሉ የኢል-78 ኤም-90 ኤ አውሮፕላኖች የአቅም ግንባታው አካል ሲሆኑ፤ አውሮፕላኖች ሳያቋርጡ በረራ ላይ እንዲቆዩና የኦፕሬሽን ክልላቸው እንዲሰፋ የሚያስችል የለውጥ አካል ነው፡፡
ይህም አየር ኃይሉ የሚያከናውናቸውን የመከላከያ ግዳጆች በተሻለ ብቃት እንዲወጣ ከማስቻሉም በላይ በራስ የመቆም አቅሙን እንዲያጠናክር መሠረት ይጥላል።
በተለይ የአውሮፕላን ጥገና፣ የቴክኖሎጂ ማሻሻያ፣ የመለዋወጫ ዕቃዎችና ሰው አልባ አውሮፕላኖችን የማምረት አቅም ማዳበር ተቋሙ ትኩረት ካደረገባቸው የለውጥ አቅጣጫዎች መካከል ይጠቀሳሉ።
ይህ እድገት ከውጭ በሚገኙ ቴክኖሎጂዎችና አገልግሎቶች ላይ ያለን ጥገኝነት ለመቀነስ፣ የሀገር ውስጥ የምህንድስና ዕውቀትን ለማሳደግና አዳዲስ የቴክኖሎጂ ክህሎቶችን ለማፍራት የሚያግዝ ነው።
የተቋሙ የሥልጠና፣ የቴክኒክና የጥገና አቅም ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር የሙያና የዕውቀት ልውውጥ በማድረግ አህጉራዊ ትብብርን ያጠናክራል።
በዚህም ኢትዮጵያ በአየር ኃይል ሥልጠና፣ በአቪዬሽን ቴክኖሎጂና በሙያዊ ልምድ ልውውጥ የአፍሪካ ትብብር መድረክ እንድትሆን ዕድል ይፈጥራል።
የተቋሙ ምህንድስና፣ የአየር በረራ ሳይንስ፣ የመረጃ ቴክኖሎጂና የማምረት አቅም መጠናከር ለወጣቶች የሙያ እድገት፣ ለምርምርና ለፈጠራ አዳዲስ አድማሶችን ይከፍታል።
በዚህ ረገድ የመከላከያ ተቋማት አቅም ግንባታ ከደህንነት ዘርፍ ባሻገር ለሀገራዊ ቴክኖሎጂ እድገትም የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ነው።
የአየር ኃይሉ ሌላው የትኩረት መስክ የአየር ጠፈር ደህንነትን ከአህጉራዊ ሰላምና ትብብር ጋር ማስተሳሰር ሲሆን፤ የአፍሪካ ሀገራት በደህንነት፣ በሰብዓዊ ቀውሶችና በተለያዩ የጋራ ተግዳሮቶች ላይ የጋራ አቅም እንዲገነቡ የሙያ ልምድና የቴክኖሎጂ ትብብር ወሳኝ ነው።
ኢትዮጵያ በዚህ መስክ ያላትን የረጅም ጊዜ ልምድ በማጋራት ለአህጉሩ የጋራ ደህንነት ጥረት አስተዋጽኦ ማበርከት ችላለች።
ይህንን አቅም በቀጣይነት ማጠናከር የሀገርን ደህንነት ከማረጋገጥ ባለፈ የቴክኖሎጂ ነፃነትን፣ የኢኮኖሚ አቅምንና የአህጉራዊ ትብብርን ያጠናክራል።
91 ዓመታትን የዘለቀው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ታሪካዊ ጉዞ የሚያሳየውም የሀገርን ሉዓላዊነት መጠበቅና የልማት አቅምን ማሳደግ ተደጋጋፊ ተልዕኮዎች መሆናቸውን ነው።
በምሕረት ደምሴ

