Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ከህዝብ ጋር በመቀናጀት በአዲሱ ዓመት የተጠናከረ የወንጀል መከላከል ስራ እንደሚሰራ ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ከመላው ማህበረሰብ ጋር በመቀናጀት በ2013 ዓ.ም የተጠናከረ የወንጀል መከላከል ስራ እንደሚሰራ ገልጿል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፈንታ÷ የሀገሪቱን ሰላምና ደህንት ለማስከበር በተለያዩ አካባቢዎች ተሰማርተው ላሉ የፖሊስ አመራሮችና አባላት እንዲሁም ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የእንኳን አደረሳቹ መልእክት አስተላልፈዋል።

ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፈንታ በመልእክታቸው፥ ኮሚሽኑ ባሳለፍነው በጀት ዓመት ከፌደራልና የክልል የጸጥታ ሃይሎች ጋር በመቀናጀት በተለያዩ አካባቢዎች ተከስተው የነበሩ ግጭቶችን በማረጋጋት፣ ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች ቶሎ ህክምና እንዲያገኙ በመስራት፣የተፈናቀሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱና ጥበቃ እንዲያገኙ የማድረግ ስራ መስራቱን ገልጿል።

በተጨማሪም የተፈጠሩ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ በመስራትና ህገ ወጥ ተግባር የፈጸሙ አካላት ወደ ህግ እንዲቀርቡ ከማድረግ ባለፈ በኮንትሮባንድ መከላከል ከ400 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ እቃዎች በገቢና ወጪ ኮንትሮባንድ በመያዝ ለመንግስት ገቢ ማድረጉን የወንጀል መከላከል ዘርፍ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፈንታ ገልፀዋል።

ምክትል ኮሚሽነር ጀነራሉ አያይዘውም የኮቪድ-19 ስርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ ህብረተሰቡ በግብይት ቦታዎችም ሆነ በመኖሪያ ቤቱ ራሱን በጠበቀ መልኩ በመንቀሳቀስ በዓሉን ማክበር እንዳለበትም ገልፀዋል።

የፖሊስ ሰራዊቱም በሚገኝባቸው በመላው የኢትዮጵያ ክፍሎች ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ተግቶ የሚሰራ በመሆኑ ማህበረሰቡ ከፀጥታ ኃይሉ ጎን በመሰለፍ ሰላምን በተጠናከረ መልኩ ማስከበር እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል።

በተጨማሪም በዓሉ በሚከበርበት ጊዜ ህብረተሰቡ ያልተፈቀዱ ተቀጣጣይና ተተኳሽ ነገሮችን ከተመለከተም ህግ የማስከበር ስራ ላይ ለተሰማሩ የጸጥታ አካላት ጥቆማ መስጠት አለበት ብለዋል።

አዲሱ ዓመት ኢትዮጵያ ከማንኛውም ወንጀል የጸዳችና ሁሉም ዜጋ ያለምንም ፍርሃትና ስጋት ተንቀሳቅሶ በመስራት ራሱን፣ ቤተሰቡንና ሀገሩን የሚለውጥበት እንዲሆን መልካም በመመኘት፤ ለስኬቱም የፀጥታ ኃይሉ ተግቶ እንደሚሰራ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል መላኩ ፈንታ ተናግረዋል።

በየደረጃ ያለው የፖሊስ አመራር አባላት በአዲሱ ዓመት ህገ መንግስቱን መሰረት በማድረግ ፖሊሳዊ ተልዕኮውን በላቀ ደረጃ ለመወጣትና የኢትዮጵያን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ከምንጊዜውም በላይ ተግተን የምንሰራበት ዓመት ይሆናል ሲሉ መግለፃቸውን ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ህዝብ ግንኙነት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

Exit mobile version