አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሶማሊያ ጦር በወሰደው እርምጃ 14 የአልሸባብ ታጣቂዎች መገደላቸው ተሰምቷል።
የጦር ሀይሉ እርምጃውን የወሰደው ከዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ በስተሰሜን 30 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ባላድ ከተማ የሽብር ቡድኑ ዛሬ ጠዋት ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ ነው ተብሏል።
የመንግስት ቃል አቀባይ እስማኤል ሙክታር ኡመር ÷ የሽብር ቡድኑ በፈጸመው ጥቃት አንድ የመንግስት ወታደር መሞቱን እና ሰባት ዜጎችም መቁሰላቸውን ነው የተናገሩት።
የአልሸባብ የሽብር ቡድንን ጥቃት ተከትሎ በባልድ ከተማ የነበረው ሁኔታ መረጋጋቱንም ቃል አቀባዩ ጨምረው ገልጸዋል።
የአልሸባብ ታጣቂዎች በባልድ ከተማ ባደረሱት ድንገተኛ ጥቃት የአካባቢውን የመንግስት ዋና መስሪያ ቤት እና የፖሊስ ጣቢያዎችን ተቆጣጥረው እንደነበረም የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የሀገሪቱ ጦር አልሸባብን ከሥረ መሰረቱ ለመንቀል በቅርብ ወራት በማዕከላዊ እና በደቡባዊ የሀገሪቱ ክልሎች ተከታታይ ዘመቻ ቢያደርግም ታጣቂ ቡድኑ የሚያደርሰውን ጥቃት አጠናክሮ መቀጠሉ ይነገራል።
ምንጭ፦ ሲ.ጂ.ቲ.ኤን
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

