አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በሐሰተኛ የብር ኖቶች እንዳይጭበረበሩ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ፖሊስ አሳሰበ።
ህብረተሰቡ ባዕድ ነገር ተቀላቅሎባቸው ከሚሸጡ ምግብና መጠጦች እንዳይታለል ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበትም ገልጿል።
ኮሚሽኑ የዘመን መለወጫ በዓል ከወንጀል የጸዳና ሰላማዊ ሆኖ እንዲከበር ዝግጅት አድርጓል።
በበዓላት ወቅት የሚፈጸም ወንጀል ቀድሞ ለመከላከልና መቆጣጠር ከህብረተሰቡ ጋር ውይይት እንዳደረገ አስታውቋል።
በኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት የሚዲያ ዲቪዥን ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ማርቆስ ታደሰ የከተማ ነዋሪዎች ግብይት በሚፈጸምበት ወቅት በሐሰተኛ የብር ኖቶች እንዳይጭበርበር ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።
ህብረተሰቡ በገበያ ቦታዎች ላይ የሀሰተኛ የብር ኖቶች ዝውውር ከተመለከተ ለፖሊስ በፍጥነት እንዲጠቆምም አስገንዝበዋል።
በበዓል ሰሞን ከሚፈጸሙ ወንጀሎች መካከል ምግብና መጠጥ ላይ ባዕድ ነገር መቀላቀል በዚህና ሌሎች በግብይት ወቅት ከሚፈጸሙ ማጭበርበር እንዲጠነቀቅ አሳስበዋል።
ህብረተሰቡ በድርጊቱ የተሰማሩ አካላትን በመጠቆም ትብብር እንዲያደርግ ዋና ኢንስፔክተር ማርቆስ ታደሰ አመልክተዋል።
የከተማውን ሰላምና ጸጥታ ለማስከበር ህብረተሰቡን ያሳተፈ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
በመዝናኛ ቦታዎች የሚፈጠሩ ጸቦችን በየመንገዱ የሚደረጉ ዝርፊያና ቅሚያዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።
በበዓል ወቅት የሚጨምረውን የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ አደጋ በሚበዛባቸው ቦታዎች የትራፊክ ፖሊሶች መሰማራታቸው ዋና ኢንስፔክተር ማርቆስ ልጸዋል።
አሽከርካሪዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለመገናኘት ባላቸው ጉጉት በፍጥነት ሲያሽከረክሩ ለአደጋ እንዳይጋለጡ በጥንቃቄና በተረጋጋ መንገድ ማሽከርከር እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከል በመዝናኛ ቦታዎች፣ በትራንስፖርት አገልግሎትና ሌሎች ሕዝብ በሚበዛባቸው ስፍራዎች ላይ የሚደረገው ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያጠናክር ተናግረዋል።
የመዲናዋ ነዋሪዎች ጥቆማ ሲኖራቸው በ011-111-01-11 እና በ991 ነጻ የስልክ መስመር እንዲሁም ለትራፊክ አደጋ 6727 ነጻ የስልክ መስመር በመደወል ማሳወቅ እንደሚችሉም ገልጸዋል።
አዲሱ ዓመት የሰላም፣የደስታ፣የስኬትና ብልጽግና እንዲሆን ዋና ኢንስፔክተር ማርቆስ ታደሰ መልካም ምኞታቸውን ማስተላለፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

