አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የ2013 አዲሱን ዓመት ምክንያት በማረግ ለ508 የህግ ታራሚዎች ይቅርታ መደረጉን የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስታወቀ።
በክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሕግ አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ንጋቱ ዓለሙ እንዳሉት፥ በክልሉ በሚገኙ ሶስቱም ማረሚያ ቤቶች ለሚገኙ 508 የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ ተደርጓል።
በክልሉ ይቅርታ ከተደረገላቸው ውስጥ 501 ወንዶች ሲሆኑ፣ 7 ደግሞ ሴቶች መሆናቸውን ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ተናግረዋል።
ይቅርታ የተደረገላቸው የሕግ ታራሚዎች፣ በማረሚያ ቤት ቆይታቸው በፈጸሙት ወንጀል የተጸጸቱና ተገቢውን ትምህርት የወሰዱ ናቸው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ ንጋቱ፥ የይቅርታ መስፈርቱን ማሟላታቸው በቦርዱ የተረጋገጠላቸው መሆናቸውን አመልክተዋል።
በይቅርታው የተካከቱት ታራሚዎች በማረሚያ ቤት ውስጥ ከ1 ዓመት ከ4 ወር አስከ 17 ዓመት ከ4 ወር ቆይታ የነበራቸው ናቸው ብለዋል።
በዓሉን ምክንያት በማድረግ ይቅርታ የተደረገላቸው 312 ከመተከል ዞን ማረሚያ ቤት፣ 69 ከካማሺ ማረሚያ ቤት እና 127ቱ ደግሞ ከአሶሳ ዞን ማረቢያ ቤት ሲሆኑ ከነገ ጀምሮ ወደ ህብረተሰቡ እንደሚቀላቀሉም ተገልጿል።
ለታራሚዎች የተደረገው ይቅርታ በማረሚያ ቤቶች ያለውን የሰው ብዛት በመቀነስ በተለይም ስርጭቱ እየጨመረ የመጣውን የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል ትልቅ ፋይዳ እንዳለው መጠቆማቸውንም ከክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

