አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦሮሚያ ክልል በ3 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር የሚከናወነው “ጉማታ ጨፌ ቱማ” የተቀናጀ ፕሮጀክት ወደ ትግበራ መሸጋገር ጀመረ።
የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊ እና ታሪካዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ታልሞ የተዘጋጀው “ጉማታ ጨፌ ቱማ” የተቀናጀ ፕሮጀክት በዛሬው እለት የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ እና በምክትል ርዕስ መስተዳድር ማእረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋ ጨምሮ ሌሎችም ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት በሱሉልታ ወረዳ ወደ ትግበራ የማሸጋጋር ሂደት ተከናውኗል።
በዛሬው እለት በተካሄደው ስነ ስርዓትም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ 40 ሴቶች በ2 ሚሊየን ብር የተገዙ ዝርያቸው የተሻሻሉ 40 ላሞች ተላልፈው ተሰጥተዋል።
እንዲሁም የጨረታ ሂደታቸው የተጠናቀቁ 5 ሞዴል ትምህርት ቤቶች ግንባታን ለማስጀመርም በክልሉ መንግስት እና በስራ ተቋራጮች መካካል ርክክብ ተካሂዷል።
በተጨማሪም ቤት መገንባት ለማይችሉ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችም በሱሉልታ ወረዳ መኖሪያ ቤት የተገነባላቸው ሲሆን፥ የተማረ ዜጋን ለማፍራት እና ሀገርን ለመገንባት የሚደረገውን እንቅስቃሴ ለመደገፍ በህብረተሰቡ ተሳትፎ የተሰበሰቡ ማጣቀሻ መጽሃፍቶችም ለወረዳዎች ተላልፈው ተሰጥተዋል።
የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፥ በዛሬው እለት ወደ ተግባር የተሸጋገረው ፕሮጀክት ጅማሮ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ግንባታቸውን ለመጀመር ርክክብ የተደረገባቸው ሞዴል ትምህርት ቤቶች ግንባታ በፍጥነት በመጠናቀቅ ለአገልግሎት መብቃት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የቤተሰብን ብልፅግና እውን ለማድረግ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሴቶችን በመለየት የወተት ላሞች እንዲሰጥ መደረጉም መልካም ተግባር መሆኑንም በማንሳት፤ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።

