Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሐረማያ ሃይቅ ውሃ መያዙን ተከትሎ ዘላቂ እንዲሆን የማፅዳት ስራ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሐረማያ ሃይቅ ውሃ መያዙን ተከትሎ ዘላቂ እንዲሆን የተለያዩ ቆሻሾችን የማፅዳት ስራ ተካሄደ፡፡

ሐረማያ ሃይቅ ከአስራ አምስት ዓመታት በላይ ደርቆ መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡

የካቲት 1996 ሙሉ ለሙሉ የደረቀው ሐይቁ በዚህ ክረምት በጣለው ዝናብ ከፍተኛ መጠን ያለው ውሃ በመያዙ የመመለስ ተስፋ ማሳየቱ ተነግሯል፡፡

ይህን ሐይቅ በዘላቂነት ጠብቆ ለማቆየት ይቻል ዘንድ የሐረማያ ከተማ ነዋሪዎች የተሳተፉበት በሃይቁ ዳርቻና ወደ ሃይቁ ውሃ የሚያስገቡ ተፋሰሶችን የፅዳት ዘመቻ አድርገዋል።

በፅዳት ዘመቻው ያገለገሉ ፕላስቲክ የውሃ ኮዳዎች ተወግደዋል ተፋሰሱንም የማፅዳት ስራ ተከናውኗል።

በፅዳት ዘመቻው የተሳተፉት የሐረማያ ከተማ ከንቲባ አቶ ሙለታ ቡሽራ ለረዥም ዓመታት ደርቆ የነበረው የሐረማያ ሃይቅ ዳግመኛ የመመለስ አዝማሚያ በማሳየቱ ዘላቂ እንዲሆን የፅዳት ዘመቻው ወሳኝነት እንዳለው ተናግረዋል፡፡

ሐይቁን ጠብቆ ለማቆየት የተለያዩ ፕላስቲኮችን መወገዳቸው ለሐይቁ ህልውና ወሳኝነት አለው ብለዋል።

የሐረማያ ሃይቅን በዘላቂነት ለማስጠበቅ በሚያስችለው የፅዳት ዘመቻ ላይ የሐረማያ ከተማ ነዋሪዎችና የሐረማያ ሆስፒታል ሰራተኞች ተሳትፈዋል።

በተሾመ ኃይሉ

Exit mobile version