አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች ኮከስ አባላት ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን መተሃራ ከተማ በትምህርት ቤት ውስጥ ተጠልለው ለሚገኙ ተፈናቃዮች 950 ሺህ ብር የሚገመት የተለያዩ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን፣ ፍራሾችንና የህጻናት አልባሳት ድጋፍ አደረጉ፡፡
ለተፈናቃይ ወገኖች የተደረገው ጊዚያዊ ድጋፍ ከተለያዩ የመንግስት ልማት ድርጅቶችና ከመንግስት ተቋማት የተሰበሰበ መሆኑን የኮከሱ ሰብሳቢ ወይዘሮ አበባዬ ገዛኸኝ ገልጸዋል፡፡
አብዛኞቹ የጉዳቱ ሰለባዎች ሴቶችና ህጻናት በመሆናቸው ለከፋ ጉዳት መዳረጋቸውንና ዘላቂ መፍትሄ እስከሚገኙ ድረስ የሁሉም ዜጋ ትብብር ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የመተሃራ ከተማ አስተዳደር ተፈናቃዮቹን ለማቋቋም የጀመረውን ጥረትም አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
መንግስት አዋሽንና የበሰቃ ሐይቅን ጨምሮ ሌሎች ወንዞች በህብረተሰቡ ላይ ጉዳት ሳያደርሱ ለልማት የሚውሉበትን መንገድ መቀየስ እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡
በአደጋው በአንድ ምሽት ብቻ 25 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ተፈናቅለው ከፍተኛ ጉዳት ሲደርስባቸው የተለያዩ ንብረቶች እንደወደሙ የመተሃራ ከተማ ከንቲባ አቶ ታደለ ድሪርሳ ገልጸዋል፡፡
ከንቲባ አቶ ታደለ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የምስራቅ ሸዋ ሀገረ-ስብከት፣ ጎንደር ዩኒቨርስቲና አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ዩኒቨርስቲ ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና ማቅረባቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

