Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማትን ትምህርት ለማስጀመር የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ስራ መሰራቱ ተገለፀ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 14 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማትን ትምህርት ለማስጀመር የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ስራ መሰራቱ ተገለፀ፡፡
የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በመከላከል የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማትን መልሶ ለመክፈት የተደረጉ ዝግጅቶችና ለወረርሽኙ የተሰጡ ግብረ-መልሶችን አስመልክቶ የምክክር መድረክ ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ ላይ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማትን ትምህርት ለማስጀመር የሚያስችለው የቅድመ- ዝግጅት ስራ እየተሰራ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዳይሬክተር ጄኔራል ዶክተር ገነነ አበበ÷ አሰልጣኞችና ድጋፍ ሰጭ ሰራተኞች ለቫይረሱ ተጋላጭ እንዳይሆኑ በፈረቃ በማሰራት የተለያዩ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል፡፡
እነዚህም የንጽህና መጠበቂያ ቁሶችን በወቅቱ የማቅረብ እና በ8 ክልሎች ከእጅ ንክኪ ነጻ የሆነ 1 ሺህ 58 በፔዳልና በሴንሰር የሚሰራ የእጅ መታጠቢያ ማሽን በማምረት ለኢንትርፕራይዞች ለማሸጋገር ተችሏል፡፡
ከዚያም ባለፈ በአንዳንድ ተቋማት ሳኒታይዘር እና ሳሙና በማምረት ለህብረተሰቡ የመደገፍ ስራ ተሰርቷል፡፡
ከ200 ሺህ በላይ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል በማምረት ለህብረተሰቡ የማቅረብ እንዲሁም ኢንተርፕራይዞችን በማብቃት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እያመረቱ ለገበያ እንዲያቀርቡ በማድረግ ተጠቀሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ተችሏል ተብሏል፡፡
በተጨማሪም በተቋማቱ ሀኪሞች የሚገለገሉበት አልባሳት መዘጋጀታቸውና ለቫይረሱ ተማሚዎች የሚያገለግል ጥራቱን የተጠበቀ 1 ሺህ 780 አልጋ በማምረት ለጤና ድርጅቶች ቀርቧል ነው የተባለው ፡፡
ስልጠና ለማስጀመርም ስለቫይረሱ ያለው ግንዛቤ እያደገ መምጣት፣ ተቋማት በራሳቸው ወረርሽኙን ለመከላከል የሚረዱ መከላከያዎችን ማምረት መጀመራቸው፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በተመለከተ የአጠቃቀም ክህሎት መዳበሩ እና የሰልጣኞች ቁጥር ውሱን መሆኑ መልካም እድሎች ናቸው ተብሏል፡፡
እንዲሁም የገጽ ለገጽ ስልጠና ለማስጀምርም የመማሪያ ክፍሎችን የማስተካከል፣ ወርክሾፖችን የማደራጀት እና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን የማሟላት ስራ በመከናወን ላይ መሆኑና ለአሰልጣኞች ግንዛቤ የመፍጠርና ቀሪ የብቃት አሀዶችን የመለየትና ፕሮግራም የማውጣት ስራ በአብዛኞቹ ኮሌጆች ተከናውኗል መባሉን ከሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
Exit mobile version