Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሱዳን ባለሃብቶች ሉኡካን አባላት ጎርጎራን ጎበኙ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሱዳን ባለሃብቶች ሉኡካን በገበታ ለሃገር ፕሮጀክት የተመረጠውን የጎርጎራ ከተማ ጎበኙ።

በገበታ ለሃገር ፕሮጀክት የተመረጠውን የጎርጎራ ከተማ የጎበኙት ልኡካን 22 አባላትን መያዙ ተሰምቷል፡፡

የሉኡካኑ መሪ ኡመር አልጋብ በጉብኝቱ ወቅት በአካባቢው አስተዳደር በህዝቡ አቀባበልና መስንተግዶ መደሰታቸውን ተናግረዋል።

የሱዳን ባለሃብቶች በኢትዮጰያ በሆቴልና ቱሪዝም እንዲሁም በኢንዱስትሪ ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸውና በእነዚህ መስኮችም ስራ ለመጀመር መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።

በተረከቧቸው ኢንቨስትመንት ቦታዎችም በፍጥነት ወደ ግንባታ በመግባት በአጭር ጊዜ አጠናቀው ለአገልግሎት እንደሚያበቁም አስታውቀዋል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወርቁ ኃይለማርያም በበኩላቸው አስተዳደሩ በጎርጎራ አካባቢ ለመዝናኛ ሎጅ ግንባታ የሚውል አስር ሄክታር መሬት ለሱዳን ባለሃብቶች ለማስረከብ ተዘጋጅቷል ብለዋል።

የጎርጎራ አካባቢ ለሆቴልና ቱሪዝም፣ አግሮ ፕሮሰሲንግ፣ መስኖ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ንብ ማነብ፣ ማዕድን ውሃና ለዓሳ ማቀነባበር ኢንቨስትመንት ምቹ መሆኑን አስታውቀዋል።

ይህንን ሀብት አቅም ባላቸው ባለሃብቶች እንዲለማ በማድረግ የአካባቢው ህብረተሰብ ተጠቃሚ እንዲሆን በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የሱዳን ባለሃብቶች በኢትዮጰያ የተለያዩ ክልሎች ዘጠኝ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ላይ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳለቸው መግለጻቸውን የተናገሩት ደግሞ የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሙሉቀን አዳነ ናቸው።

ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከልም ሁለቱ በአማራ ክልል በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክና በጎርጎራ ሆቴልና ቱሪዝም የሚከናወኑ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ሳንቃ በር ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ዘመናዊ የቱሪስት መዳረሻ ሎጅ ለመገንባት ቦታ መረከባቸውንም አስታውቀዋል።

ግንባታውን በመጪው ጥቅምት ወር በመጀመር መጋቢት ወር 2013 ዓ.ም በማጠናቀቅ ወደ ስራ እንደሚገቡ እንደሚጠበቅ ኢዜአ ዘግቧል።

የሱዳን ልኡካን አባላት በጎንደርና አካባቢው የሦስት ቀናት ቆይታ በማድረግ ልዩ ለዩ የኢንቨስትመንት አማራጮችን የተመለከተ ሲሆን ወደ ባህር ዳር ከተማ እንደሚያቀኑ ይጠበቃል።

Exit mobile version