Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ፖሊስ የመስቀል ደመራና ኢሬቻ በዓላት በሰላም እንዲከበር አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፌደራል ፖሊስ የመስቀል ደመራና ኢሬቻ በዓላት በሰላም እንዲከበር አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ፡፡
በዓላቱን አስመልክቶ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጀነራል እንደሻው ጣሰው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫው የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጀነራል እንደሻው ጣሰው እንዳሉት÷ ፖሊስ በዓላቱ በሰላም እንዲከበር ለማድረግ ከህብረተሰቡ ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ሁለቱን በዓላት ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ እንዴት መከበር እንዳለበት አስቀድሞ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያት ከስምምነት መደረሱን ገልፀዋል።
በመሆኑም በዓሉ በሚከበርበት አካባቢ የሚገኝ ማንኛውም አካል የይለፍ ወረቀት ወይም ባጅ ይዞ መገኘት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡
ይሄን ያልያዘ አካልም ወደ ክብረ በዓሉ ቦታ እንደማይገባ ነው የተናገሩት፡፡
ፖሊስ ይህንንም ለማስፈፀም ከሚመለከተው አካላት ጋር በመተባበር ለመስራት ዝግጅቱን አጠናቋል ያሉ ሲሆን ከዚህ ጋር ተያይዞ ተመሳሳይ ባጅ አሰርቶ ለመግባት የሚሞክር ካለ ፖሊስ ጥብቅ ፍተሻና ልየታ አድርጎ እርምጃ ይወስዳል ብለዋል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞም የመስቀልና የኢሬቻ በዓላት ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዳይከበር ለማድረግ የሚንቀሳቀሱ አካላት እንዳሉ ፖሊስ ደርሶበታል ብለዋል ኮሚሽነር ጀነራሉ፡፡
የፌደራል ፖሊስ በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ ለማድረግ በቂ ዝግጅት አድርጎ ወደ ስራ መግባቱንም ገልፀው ይህን መነሻ በማድረግም በአዲስ አበባ ሁሉም መግቢያ በሮች ጥብቅ ፍተሻ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ከመስከረም 25 በኋላ መንግስት የለም በሚል ህዝቡን ለአመፅ እንዲነሳሳ የሚያደርጉ መልዕክቶችን በስፋት የሚያሰረጩ አካላት እንዳሉም ኮሚሽነር ጀነራል እንዳሸው ጠቁመዋል፡፡
በዚህም ሀገር ለማፍረስ የሚንቀሳቀስን ማንኛውምን አካል ፖሊስ እንደማይታገስና ህግ የማስከበር ስራውን አጠናክሮ እንደሚሰራ አስረድተዋል፡፡
በመሆኑም ህብረተሰቡ በዚህ ያልተገባ ጥሪ ሳይወናበድ የአካባቢውን ሰላም እንዲጠብቅ አሳስበዋል፡፡
በሃይለሚካኤል ዴቢሳ
Exit mobile version