Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአዲስ አበባ ሰላም ምክር ቤት ለደመራ፣ መስቀልና ኢሬቻ በዓላት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፈ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ሰላም ምክር ቤት ለደመራ፣ መስቀልና ኢሬቻ በዓላት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፈ፡፡
 
ምክር ቤቱ በዓላቱን በማስመልከት በዛሬው ዕለት መግለጫ ሰጥቷል፡፡
 
በመግለጫው በቅርቡ የተቋቋመው የአዲስ አበባ ምክር ቤት ለሰላም እና የህዝቦች አብሮነት መቀጠል የሚረዱ የተለያዩ ጥናቶችን እየሰራ መሆኑን አንስቷል፡፡
 
እንዲሁም ከአዲስ አበባ ከተማ ክፍለ ከተሞች ከተውጣጡ አካላት ጋር በመሆን የተለያዩ ለሰላም የሚበጁ ስራዎች እየሰራ እንደሚገኝ ነው የገለጸው፡፡
 
በነገው ዕለት እና በቀጣይ ሳምንት የሚከበሩት የደመራ፣ መስቀልና የኢሬቻ በዓላት በሰላማዊ መንገድ እንዲከበሩ አሳስቧል፡፡
 
ምክር ቤቱ ህብረተሰቡ በዓላቱን በሚያከብርበት ወቅት ለዓለም ስጋት ከሆነው የኮሮና ቫይረስ እየተጠነቀቀ መሆን እንዳለበትም አንስተዋል፡፡
 
በተጨማሪም በዚህ ወቅት የጤና ሚኒስቴር የሚያወጣቸውን መመሪያዎች መከተል እንደሚገባም አሳውቋል፡፡
 
በጸጋዬ ንጉስ
Exit mobile version