Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአማራ ክልል መንግሥት በክልሉ ለሚገኙ 815 የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአማራ ክልል መንግሥት በክልሉ ለሚገኙ 815 የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ።
የክልሉ መሥተዳድር ምክር ቤት ዛሬ መስከረም 16 ቀን 2013ዓ.ም ባካሄደው 5ኛ ዙር 6ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ስብሰባ በክልሉ ይቅርታ አሰጣጥ መሠረት ለታራሚዎቹ ይቅርታ እንዲደረግ ውሳኔ አሳልፏል።
በክልሉ ማረሚያ ቤቶች ለሚገኙ 815 የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ ማድረጉን አስታውቋል፡፡
የአማራ ክልል ይቅርታ ቦርድ የይቅርታ መስፈርቱን ያሟሉ በክልሉ የሚገኙ ታራሚዎችን የይቅርታ ጥያቄ በመመርመር ለአማራ ክልል መሥተዳድር ምክር ቤት በማቅረብ በክልሉ ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ ታራሚዎች የይቅርታው ተጠቃሚ በመሆን የወንጀል አስከፊነትን በማወቅና በመታራም ወደ ኅብረተሰቡ ተቀላቅለው የበደሉትን ሕዝብ በልማትና በሀገር ግንባታ ላይ የራሳቸውን አስተዋጽኦ በማበርከት እንዲክሱ በይቅርታ እንዲፈቱ መወሰኑን በአብድመ ዘግቧል።
በክልሉ ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ ይቅርታ የሚያሰጡ የእስራት መስፈርቶችን ያሟሉ 756 ወንዶች፣ 13 ሴቶች በድምሩ 769 ሰዎች እንዲሁም ይቅርታ የሚያሰጥ የዕድሜ መስፈረትን ያሟሉ 16 ወንዶች ፣ ይቅርታ የሚያሰጥ የጤና መስፈረትን ያሟሉ 9 ወንዶች እና የፆታ መስፈርትን በተመለከተ 2 ሕጻናትን ይዛ የታሰራች 1 ሴት ይቅርታ ተደርጎላቸዋል።
ከሌላ ክልል በዝውውር የመጡና መስፈርቱን የሚያሟሉ ወንድ 20 ፣ በአጠቃላይ ወንድ 801 ሴት 14 ድምር 815 ታራሚዎች የክልሉ ይቅርታ ቦርድ የቀረበውን ማስረጃ መርምሮ ይቅርታ እንዲደረግ ለአማራ ክልል መሥተዳድር ምክር ቤት ባቀረበው የውሳኔ ሐሳብ መሠረት ነው ታራሚዎቹ የይቅርታው ታጠቃሚ እንዲሆኑ የተወሰነው፡፡
የሕግ ታራሚ የይቅርታ ተጠቃሚ ሊሆን የሚችለው በተከሰሰበት ወንጀል አጠቃላይ የክርክር ሂደቶችን ጨርሶ ወንጀል መፈፀሙ በቀረቡበት ማስረጃዎች ተረጋግጦ ጥፋተኛ ተብሎ ተገቢው ቅጣት ተወስኖበት ቅጣቱን በማረሚያ ቤት በመፈጸም ላይ የሚገኝ ታራሚ ሲሆን ይኸውም ታራሚ የወንጀል አስከፊነትን አውቆ፣ በፈፀመው ወንጀል ታርሞና ተፀፅቶ፣ የበደለውን ክሶ መልካም ዜጋ መሆኑ የተረጋገጠለት ሰው ብቻ ነው ተብሏል፡፡
Exit mobile version