Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አርሶ አደሩን በዘላቂነት ተጠቃሚ የሚያደርጉ አሰራሮች እንደሚዘረጉ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ገለጹ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 18 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) አርሶ አደሩን በዘላቂነት ተጠቃሚ የሚያደርጉ አሰራሮች እንደሚዘረጉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ከተለያዩ ክፍለ ከተሞች ከተውጣጡ የአርሶ አደር ተወካዮች ጋር ውይይት አካሂደዋል፡፡

በውይይቱ ወቅትም በተለያዩ ጊዜያት በልማት ሳቢያ በርካታ አርሶ አደሮች ለማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ እና ስነልቦናዊ ችግሮች መዳረጋቸውን ምክትል ከንቲባዋ ተናግረዋል፡፡

ከቀያቸው የተፈናቀሉ አርሶ አደሮችን እና የአርሶ አደር ልጆችን በተገቢው መንገድ በማጣራት በዘላቂነት የሚቋቋሙበትን ሁኔታ ለመፍጠር የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርግም ነው የተናገሩት፡፡

አርሶ አደሩን ሽፋን በማድረግ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በምንም ሁኔታ ተቀባይነት እንደሌላቸው ጠቅሰው በአርሶ አደር እና በአርሶ አደር ልጆች ስም መሬት የሚዘርፉ ደላሎች እና ህገወጦች ላይ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወሰድ ገልጸዋል፡፡

ከአርሶ አደሮች በተጨማሪ መላው የከተማዋን ነዋሪዎች በልማቱ ተሳታፊ እና ተጠቃሚ ለማድረግ ልዩ ልዩ አሰራሮች ይዘረጋሉም ነው ያሉት፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በልማት ተነሺ የሆኑ አርሶ አደሮችን መልሶ ለማቋቋም የተዘረጋ አሰራርና አደረጃጀት ላይ ምክትል ከንቲባዋ፣ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ ዓለሙ እና በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ በልማት ተነሺ ከሆኑ አርሶ አደር ተወካዮች ጋር ውይይት አድርገዋል።

በህጋዊ አሰራር በልማት ለተነሱ አርሶ አደሮች እና የአርሶ አደር ልጆች ከመጭው ሀሙስ ጀምሮ የጋራ መኖሪያ ቤት የማስተላለፍ ስራ እንደሚከናወን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version