አዲስ አበባ ፣ መስከረም 19 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአቶ ልደቱ አያሌውን የ100 ሺህ ብር ዋስትና ትዕዛዝን ያገደው የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በምስራቅ ሸዋ ዞን ተዘዋዋሪ ምድብ ችሎት ዛሬ ክርክር የተካሄደበት የዋስትና ጥያቄ ላይ ብይን ለመስጠት ለመሰከረም 26 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ።
አቶ ልደቱ አያሌው በአዳማ ከተማ የሚገኘው የምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተከሰሱበት ህገወጥ የጦር መሳሪያ ይዞ መገኘት ወንጀል ዋስትና አያስከለክለውም ሲል የ100 ሺህ ብር ዋስ አስይዘው እንዲወጡ ትዕዛዝ የሠጠ ቢሆንም÷ የአዳማ ፍትህ ቢሮ አቃቤ ህግ ይግባኝ ማለቱን ተከትሎ ዋስትናው እግድ ተጥሎበት ነው ለዛሬ ተለዋጭ ቀጠሮ የተሰጠው።
በዚህም ቀጠሮ በአቶ ልደቱ በኩል ዋስትናው ሊታገድ አይገባም ዋስትናም የሚያስከለክል አይደለም የሚሉ መቃወሚያዎች ተነስተዋል።
በአቃቤ ህግ እና በአቶ ልደቱ ጠበቆች መካከል የዋስትና ክርክር የተደረገ ሲሆን÷ ክርክሩን ያዳመጠው ፍርድ ቤቱም ለመስከረም 26 ብይን ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በተከሰሱበት ህገወጥ የጦር መሳሪያ ይዞ መገኘት ክስን በተመለከተም ለነገ በአዳማ ከተማ ምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀጠሮ መያዙ የሚታወስ ነው።
በታሪክ አዱኛ
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

