Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሀረሪ ክልል የአርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ የተለያየ ጉዳት ያደረሱ 88 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ተከፈተ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 19 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሀረሪ ክልል የአርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በክልሉ በሰው አካልና ንብረት እንዲሁም ቅርስ ላይ ጉዳት እንዲደርስ ባደረጉ 88 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ መክፈቱን የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አስታውቋል።
የክልሉ ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በክሪ አብደላ ÷ የፌዴራል እና የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የምርመራ ቡድን በተደራጀና በተቀናጀ ሁኔታ የምርመራና የማጣራት ስራ ሲያከናውን ቆይቷል ብለዋል።
በዚህም የአርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በክልሉ በሰው አካልና ንብረት እንዲሁም በሁለት ሀውልቶች ላይ ጉዳት እንዲደርስ ባደረጉ 88 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ መክፈቱን ተናግረዋል።
ከእነዚህም ውስጥ 63ቱ በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆኑ ቀሪዎቹ ደግሞ በሀረሪ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ክስ እንደተመሰረተባቸው ገልጸዋል።
በክልሉ ወንጀልን በመከላከልና ተጠርጣሪዎችን በማጋለጥ ረገድ ህብረተሰቡ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ÷ ይህ ተግባር በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል ይገባል ብለዋል።
ሃላፊው አያይዘውም የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በቀጣይም ህግን የማስከበርና የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ስራውን አጠናክሮ ይቀጥላም ብለዋል።
ተከሳሾቹም መስከረም 19 ቀን 2013 ዓ.ም ከሰአት በኋላ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ችሎት ቀርበው ክሳቸው እንደሚሰማ መጠቆማቸውን ከክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዬች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።
Exit mobile version