Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ም/ከ አዳነች አቤቤ ከአዲስ አበባ ኦሮሚያ ወጣቶች ማህበር ጋር በኢሬቻ በዓል አከባበር ዙሪያ ውይይት አካሄዱ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከአዲስ አበባ ኦሮሚያ ወጣቶች ማህበር ጋር በኢሬቻ በዓል አከባበር ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡

በድምቀት የሚከበረው የኢሬቻ በዓል ዘንድሮ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በውስን ሰዎች እንዲከበር የአባገዳዎች ህብረት ባስቀመጡት አቅጣጫ መሠረት እንደሚከበር ነው የተገለጸው፡፡

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት ወጣቶች በአባገዳዎች የኢሬቻ በዓል በውስን ሰው እንዲከበር ለምን እንደተደረገ እና ሌሎች ክብረበዓሉን የሚመለከቱ ጥያቄዎችን ለምክትል ከንቲባ አዳነች አቅርበዋል፡፡

ወይዘሮ አዳነችም ከወጣቶቹ ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የሰላም፣ የፍቅር፣ የእርቅ እና የመቻቻል ተምሳሌት በሆነው የኢሬቻ በዓል ላይ ሁሉም የኦሮሞ ህዝብ መገኘት ይፈልጋል ያሉት ወይዘሮ አዳነች ወቅቱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ ያለበት በመሆኑ አባገዳዎች ባስቀመጡልን አቅጣጫ መሠረት በዓሉን ማክበር ይኖርብናል ብለዋል፡፡

ምክትል ከንቲባዋ ወጣቱ የሰላም ዘብ በመሆን በዓሉ በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ ለማስቻል ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በትብብር እንዲሰራም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በዓሉ ላይ የሚታደሙ የህብረተሰብ ክፍሎችም በጤና ባለሞያዎች በተቀመጠው መመሪያ መሠረት ራሳቸውን ከኮቪድ-19 በመጠበቅ ማክበር እንዳለባቸውም ወይዘሮ አዳነች ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም በውይይቱ ላይ ለተሳተፉት ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እና አቶ ማሾ ኦላና የባህል ልብስ ሽልማት ከወጣቶቹ እንደተበረከተላቸው ተገልጿል፡፡

 

 

 

Exit mobile version