Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአሜሪካ አቪየሽን ባለስልጣን ኃላፊ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን አሁንም ማስተካከል የሚገባው ጉዳይ እንዳለ ተናገሩ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአሜሪካ ፌደራል አቪየሽን ባለስልጣን ኃላፊ ስቲቭ ዲክሰን ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላንን አሁንም ማስተካከል የሚገባው ጉዳይ እንዳለ ገለጹ፡፡

ስቲቭ ዲክሰን ይህንን ያሉት ባልተለመደ መልኩ አውሮፕላኑን ማብረራቸውን ተከትሎ ነው ተብሏል፡፡

የቀድሞው አብራሪ ዲክሰን ሲያትል ከሚገኘው የቦይንግ ማዕከል በመነሳት ለሁለት ሰዓታት ማብረራቸው ነው የተነገረው፡፡

ባካሄዱት በረራ መደሰታቸውን የገለጹት ዲክሰን ለኩባንያው የሚያቀርቡት ጥያቄም እንዳለ ጠቁመዋል፡፡

ዲክሰን ኩባንያው ያስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሆን ቅድመ ሁኔታዎቹን የገለጹበት መንገድ መቀየር ይገባዋል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ዲክሰን መሻሻል የሚገባው ጉዳይ አለ ቢሉም በትክክል ይህ ነው ብለው ለይተው አለመናገራቸው ተገልጿል፡፡

የፌደራሉ ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ኩባንያው ያቀረበውን የደህንነት መመሪያ እየገመገመ መሆኑም ተነግሯል፡፡

የቦይንግ ምርት የሆነው 737 ማክስ አውሮፕላን በኢንዶኔዢያ እና በኢትዮጵያ መከስከሱን ተከትሎ ከበረራ ደህንነት ጋር በተያያዘ ከበረራ ውጪ መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡

ባለፉት ሳምንታትም የአሜሪካ ምክር ቤት በተከሰከሱት ሁለት ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ዙሪያ ቦይንግና የፌደራል አቪዬሽን ባለስልጣን አካላትን ተጠያቂ አድርጓል፡፡

ምርመራውን ለ18 ወራት ሲያካሂድ የቆየው የአሜሪካ ምክር ቤት ቦይንግ ቴክኒካል የሆኑ ጉዳዮችን ለማጋራት ዳተኛ ነበር ብሏል፡፡

ምክርቤቱ በግኝቱ ቦይንግ በማክስ ዲዛይንና ልህቀት ላይ ችግር እንደነበረበት በምርመራው ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡

ከበረራ ውጪ በሆነባቸው 18 ወራት ውስጥ ከ18 ቢሊየን ዶላር በላይ ማጣቱን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ምንጭ፡-ሲ ኤን ኤን

 

Exit mobile version