አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአውሮፓ ህብረት ቱርክ በሜዲትራንያን ባህር በምታደርገው የጠብ አጫሪነት ድርጊት ሳቢያ ማዕቀብ ሊጥል እንደሚችል አስጠነቀቀ፡፡
የህብረቱ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ኧርሱላ ቮን ደር ለየን ቱርክ በምስራቅ ሜዲትራንያን ከምታከናውነው የተናጠል እንቅስቃሴ እንድትታቀብ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ፕሬዚዳንቷ ማስጠንቀቂያውን ያሰሙት የህብረቱ ሃገራት አመራሮች በቤላሩስ ጉዳይ ላይ ለመምከር በተሰባሰቡበት ወቅት ነው ተብሏል፡፡
አሁን ላይ በአካባቢው በግሪክና በቱርክ መካከል ያለው ውጥረት እያየለ መምጣቱ ይነገራል፡፡
በአካባቢው ያለው የሃይል ሃብትና የባህር ላይ ድንበር ለሃገራቱ የፍጥጫ ምክንያት መሆኑም ነው የሚነገረው፡፡
ቱርክም በአካባቢው ያለውን የነዳጅና የጋዝ ክምችት ለማጥናት በሚል በተደጋጋሚ ቃኝ መርከቦች ልካለች፡፡
ይህን ተከትሎም ከግሪክ ጋር እሰጣገባ ውስጥ ገብተዋል፡፡
ፕሬዚዳንቷ ህብረቱ ከቱርክ ጋር መልካም ግንኙነት መመስረት እንደሚፈልግ ገልጸዋል፡፡
ሆኖም ግንኙነቱ በቱርክ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ነው በማለት ተናግረዋል፡፡
ምንጭ፡-ቢቢሲ

