አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ስድስተኛ ሃገራዊ ምርጫን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኀን የደረሰበትን አስጎብኝቷል፡፡
ቦርዱ በጉብኝቱ በስድስተኛው ሃገራዊ ምርጫ 50 ሚሊየን መራጮች ድምጽ ይሰጣሉ ተብሎ እንደሚጠብቅ ነው የገለጸው፡፡
እንዲሁም ለ50 ሺህ 900 የምርጫ ጣቢያዎች የሚሆኑ መዝገቦች ዝግጁ መሆናቸውንም ጠቅሷል፡፡
በተጨማሪም ለመራጮች ምዝገባ የሚያከናውኑ 152 ሺህ 700 አስፈጻሚዎችና ለድምጽ መስጫ ቀን ደግሞ 254 ሺህ 500 አስፈጻሚዎች ዝግጁ መሆናቸውም ነው የተገለጸው፡፡
እንዲሁም ለመራጮች ምዝገባ የተዘጋጁ የተለያዩ ቁሳቁሶችም በጉብኝቱ ወቅት ለሚዲያ አካላት አስጎብኝቷል፡፡
ከቁሳቁሶቹ መካከል በአምስት ቋንቋዎች የተዘጋጁ የመራጮች መዝገቦች፣ የደህንነት መጠበቂያ ያለው የተመዘገቡ የመራጮች ካርድ፣ ለአስፈጻሚዎች የሚውሉ ቁሳቁሶች ያሉት ሰማያዊ ሳጥን፣ የደህንነት መጠበቂያ ቁልፍ፣ መከፈታቸውን የሚያስታውሱ ቦርሳዎች እና የጠረጴዛ ባትሪ በጉብኝቱ ተካተዋል፡፡
በግልጽ የሚያሳዩ የድምጽ መስጫ ሳጥኖች፣ የሚስጥር ድምጽ መስጫ መከለያዎች እና ማስፈጸሚያ ቁሳቁስ የያዘ ሰማያዊ ሳጥን ይገኙበታል፡፡
በግልጽ የሚያሳዩ የድምጽ መስጫ ሳጥኖች 207 ሺህ ሲሆን አንድ ጣቢያ አራት ድምጽ መስጫ ድረስ ይኖረዋል ተብሏል፡፡
በኃይለየሱስ ስዩም

