Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ በሳዑዲ ለችግር የተጋለጡ ዜጎች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ጥረቷን አጠናክራ ትቀጥላለች-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ ሳዑዲ አረቢያ የሚኖሩና ለችግር የተጋለጡ ዜጎች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር መስራቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ በኢትዮጵያ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከተከሰተ ጀምሮ በመጀመሪያው ዙር በተደረገ የማስመለስ ስራ በሳኡዲ አረቢያ ይኖሩ የነበሩና ለከፍተኛ ችግር የተጋለጡ 3 ሺህ 500 ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መደረጉን ገልጿል፡፡

በተመሳሳይ በሁለተኛው ዙር 2 ሺህ ኢትዮጵያዊያንን ከሳኡዲ አረቢያ ለማስመለስ ታቅዶ እስከዛሬ 964 ዜጎች ተመልሰዋል ብሏል።

እንዲሁም የሳኡዲ አረቢያ መንግስት በመጋቢት ወር 2009 ዓም ያለህጋዊ ሰነድ የሚኖሩ የውጭ አገር ዜጎች በ90 ቀናት ውስጥ አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ባስቀመጠው የጊዜ ገደብ መሰረት፤ የኢትዮጵያ መንግስት ከግንቦት 2009 ዓም ጀምሮ በአገራችን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እስከተከሰተበት ድረስ በሳኡዲ አረቢያ ያለህጋዊ ሰነድ ይኖሩ የነበሩ እስከ 400ሺህ የሚደርሱ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ አድርጓል።

ሆኖም በህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች አማካኝነት ከተመለሱት ዜጎች ውስጥ በርካቶቹ በድጋሚ ያለህጋዊ ሰነድ ወደ ሳኡዲ አረቢያ በመጓዛቸው ለከፍተኛ ችግር የተጋለጡ በርካታ ኢትዮጵያን እንደሚገኙ ሚኒስቴሩ ገልጿል።

በዚህም የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎች ተገቢውን ክብር እንዲያገኙና አስፈላጊው ድጋፍ ተደርጎላቸው እንዲኖሩ፤ ወደ አገራቸው ለመመለስ የሚፈልጉ ደግሞ ተገቢው ዝግጅት ተደርጎ እንዲመለሱ ከሳኡዲ አረቢያ መንግስት ባለስልጣናት እና በጉዳዩ ላይ ከሚሰሩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በየጊዜው ተከታታይ ውይይቶችን በማድረግ አበረታቸ ውጤቶች እንደተገኙ አንስቷል፡፡

መንግስት የሚያደርገውን ትብብርና ጥረትም አጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለፁን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘና መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version