አዲስ አበባ ፣ መስከረም 23 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሆስፒታል ገቡ፡፡
ከነጩ ቤተ መንግስት የወጡ መረጃዎች ፕሬዚዳንቱ መጠነኛ የድካም ስሜት እንዳለባቸው ያመላክታሉ፡፡
ይሁን እንጅ ትራምፕ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ የጠቀሰው መረጃው ለተሻለ ክትትልና ጥንቃቄ ሲባል ሆስፒታል መግባታቸውን አመላክቷል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ከነጩ ቤተ መንግስት በሄሊኮፕተር ወደ ዋልተር ሪድ ሆስፒታል አቅንተዋል፡፡
በወቅቱም ለወትሮው የሚሳለቁበትን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ አድርገው የታዩ ሲሆን፥ አውራ ጣታቸውን በማንሳት ደህና ነኝ የሚል ምልክት አሳይተዋል፡፡
በቪዲዮ በለቀቁት መልዕክትም “ደህና ነኝ ብየ አስባለሁ፤ ነገሮች በጥሩ ሁኔታ እንደሚሄዱም እገምታለሁ ባለቤቴም ደህና ናት” በማለት ከጎናቸው ለሆኑት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ የተወሰነ የቫይረሱን ምልክት ከማሳየታቸው ውጭ በመልካም ጤንነት ላይ በመሆናቸው በሆስፒታሉ ውስጥ ሆነው ሀገራቸውን እየመሩ ይቀጥላሉም ነው የተባለው፡፡
ትራምፕ በሙከራ ላይ የሚገኝ መድሃኒት የወሰዱ ሲሆን ተጨማሪ ቪታሚኖችን ጨምሮ ከቫይረሱ ለማገገም የሚረዱ ቀላል መድሃኒቶችን ወስደዋል ተብሏል፡፡
በህዳሩ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የእርሳቸው ተቀናቃኝ የሆኑት ጆ ባይደን ትራምፕና ባለቤታቸው ከቫይረሱ በቶሎ ያገግሙ ዘንድ ተመኝተዋል፡፡
ምንጭ፦ ቢቢሲ

