አዲስ አበባ ፣ መስከረም 23 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት አንድ አካል የሆነው የጎርጎራ ልማት ፕሮግራምን የተመለከተ ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱ ላይ አማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አቶ ተመሥገን ጥሩነህን ጨምሮ የሳይንስና ኢኖቬሽን ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ ፣ የፌዴራል መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ እና የክልልና የፌዴራል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ከውይይቱ አስቀድሞም በከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎቹ ለልማት የተመረጡ ቦታዎች የመስክ ምልከታ ተደርጓል።
በዚህም በአካባቢው አራት ሺህ ሄክታር ስፋት ያለውንና ለመስኖ ልማት የሚያገለግለውን መሬት ጎብኝተዋል።
በውይይቱም በቀጣይ ደረጃ በደረጃ ሊከወኑ የሚገባቸው ተግባራት ምን ሊሆኑ እንደሚገባም ተነስቷል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ÷ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች በሀገሪቱ ያሉ የልማት እንቅስቃሴዎች የሚያነቃቁ ናቸው ብለዋል።
አቶ ተመስገን አያይዘውም ክልሉም ወደ ጎርጎራ ለሚመጡ አልሚዎች አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ በበኩላቸው÷ የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች ግዙፍና አለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው በመሆናቸው የመሰረተ ልማት አቅርቦቶች በፍጥነት ሊከናወኑ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ ÷ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃሳብ የሚተገበሩት የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች የተለየና የአለምን ቀልብ የሚስቡ ሃሳቦችን ይዘው የሚመጡ ባለሃብቶችን በመምረጥ ማስተናገድ ይገባቸዋል ብለዋል።
አያይዘውም የፕሮጀክቶቹ አፈፃፀምም ፈጣንና ከቢሮክራሲ የፀዳ ሊሆን ይገባልም ነው ያሉት።
የገበታ ለሀገር ጎርጎራ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ዶክተር ፍስሃ አሰፋ በውይይቱ ወቅት እንደገለፁት÷ ከዚህ በፊት አዲስ አበባ ላይ የተሰሩ ፕሮጀክቶችን ተሞክሮ በመያዝ በሶስት አካባቢዎች የገበታ ለሃገር አላማን የያዙ ልማቶች እንደሚፈፀሙ ተናግረዋል።
ከእነዚህም መካከል አንዷ የሆነችውን ጎርጎራንም ታሪክና ባህሏን ከተፈጥሮ ይዘቶች ጋር ጠብቆ በተለየ ገፅታ ለማልማት ዝግጅቶች እየተደረጉ ናቸው ብለዋል።
በሙሉጌታ ደሴ
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

