አዲስ አበባ፣መስከረም 26፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኮሮና ቫይረስ የተያዙት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሦስት ቀናት የሆስፒታል ቆይታ በኋላ ወደ ዋይት ሐውስ ተመልሰዋል፡፡
የህክምና ክትትላቸውንም በዋይት ሐውስ ውስጥ ይቀጥላሉ ነው የተባለው፡፡
በቤተመንግስቱ ውስጥ የሚገኙ ሐኪሞችም ትራምፕ ዴክሳሜታሶን እየወሰዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ከሆስፒታል መውጣታቸውን አስመልክቶ የትዊተር መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም ከ20 ዓመታት በፊት ይሰማኝ ከነበረው ደህንነት ይልቅ አሁን የበለጠ ጤንነት ይሰማኛል ሲሉ ጽፈዋል፡፡
እንዲሁም ቫይረሱን እንዳትፈሩት እንዲቆጣጠራችሁም አትፍቀዱለት ብለዋል፡፡
በዚህ ንግግራቸውም ፕሬዚዳንቱ ነገሩን አጥብቀው አልያዙትም ተብለው ትችት እየቀረበባቸው ይገኛል።
የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛም በትክክል እየተጠቀሙ አይደለም ነው የተባለው፡፡
በቤተመንግስቱ ውስጥም በርካታ ረዳቶቻቸው በኮሮና ቫይረስ መያዛቸውም ተሰምቷል፡፡
ተቀናቃኛቸው ጆ ባይደን÷ ትራምፕ በመልካም ጤንነት ወደ ዋይት ሐውስ በመመለሳቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ባይደን ከመልካም ምኞታቸው በተጨማሪ ትራምፕ ላይ ያላቸውን ወቀሳ አቅርበዋል፡፡
ቫይረሱ የተገኘበት ሰው መፈጸም የሚገባውን ጥንቃቄ ካላሟሉ ኃላፊነቱ እንደሚወስድም ነው የገለጹት፡፡
በትራምፕና በባይደን መካከል የሚካሄደው የአሜሪካ የ2020 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ 27 ቀናት ቀርተውታል፡፡
ምንጭ፡ ቢቢሲ

