Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሦስት ተመራማሪዎች ስለ ጨለማ ሽንቁር (ብላክ ሆል) ባካሄዱት ጥናት በፊዚክስ ዘርፍ የኖቤል ሽልማትን አሸነፉ

አዲስ አበባ፣መስከረም 26፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በዘንድሮው የፊዚክስ የኖቤል ሽልማት ዘርፍ በጨለማ ሽንቁር ወይንም ብላክ ሆልን ለመረዳት ባካሄዱት ጥናት ሶስት ተመራማሪዎች ተሸላሚ ሆነዋል፡፡
 
ሦስቱ ተመራማሪዎች የጨለማ ሽንቁርን(ብላክ ሆልን) ለመረዳት ባካሄዱት ጥናት ነው ሊሸለሙ የበቁት ተብሏል፡፡
 
ሽልማቱን በጋራ ያሸነፉት ትውልደ እንግሊዛዊው ሰር ሮጀር ፔንሮስ፣ ሬይንሃርድ ጌንዘል እና ፕሮፌሰር አንድሬ ጌሄዝ ናቸው፡፡
 
ሰር ሮጀር ከተበረከተው 1 ሚሊየን 120 ሺህ 867 ዶላር ሽልማት ውስጥ ግማሹን ሲቀበሉ ቀሪውን ሁለት የሙያ አጋሮቻቸው ይወስዳሉ ነው የተባለው፡፡
 
ከአውሮፓውያኑ 1901 ጀምሮ 200 የፊዚክስ ሊቆች የሎሬትነት ማዕረግ ማግኘታቸውን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
 
ከ200 ተሸላሚዎች መካከልም በዘንድሮው የፊዚክስ ዘርፍ የኖቤል ተሸላሚ የሆኑት ፕሮፍሰር አንድሬ ጌሄዝ አራተኛዋ ሴት መሆናቸው ተሰምቷል፡፡
 
የጨለማ ሽንቁር ወይንም ብላክ ሆል ከፍተኛ የሆነ የስበት ኃይል ያለው መሆኑ ይነገራል፡፡
 
ከፍተኛ በሆነው የስበት ኃይሉ አማካኝነትም ብርሃንን እንኳ አያሳልፍም ይላሉ አጥኚዎቹ፡፡
 
እኛ በምንኖርበት ህዋ ውስጥ መጠናቸው የተለያየ በርካታ ብላክ ሆሎች መኖራቸውንም ተመራማሪዎቹ ይገልጻሉ፡፡
 
የኖቤል ሽልማት በየዓመቱ ታላላቅ ስራ ላበረከቱ ሰዎች የሚሰጥ ሲሆን የኬሚስቱ ሊቅ አልፍሬድ ኖቤል ከመሞቱ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ በ1895 ነበር የመሰረተው፡፡
 
ምንጭ፡-ቢቢሲ
Exit mobile version