አዲስ አበባ ፣ መስከረም 26 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)በአዲስ አበባ ከተማ ለተማሪዎች የሚሆን 5 ሚሊየን የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭብሎችን ጨምሮ ሌሎች ቁሳቁሶች ከተለያዩ ድርጅቶች ድጋፍ ተደረገ፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ለተማሪዎች ምገባ ፣ የትምህርት ቁሳቁስ ፣ቦርሳ እና ጫማ እንዲሁም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንዳይጋለጡ የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭብሎች ለማቅረብ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮችን በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
ይህን ተከትሎ የተለያዩ ድርጅቶች በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ እና ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ድጋፍ አድርገዋል፡፡
በዚህም ጉያ ቴክስታይል ጋርመነት ደረጀውን የጠበቀ 5 ሚሊየን ሜዲካል የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭብሎች ድጋፍ አድርጓል፡፡
ጤናችን በእጃችን (safe hands)ለሁሉም የመንግስት ትምህርት ቤቶች የሚሆን 3 ሺህ የውሃ ማጠራቀሚያ ሮቶዎችን ድጋፍ ማድረጉ ነው የተገለፀው፡፡
እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ የአካባቢ ጥበቃ እና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽን በከተማዋ የሚገኙ ማዕድን አልሚዎችን በማስተባበር አንድ ጫማ ለአንድ ተማሪ በሚል የ300 ሺህ ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ በርክክቡ ወቅት ቁሳቁሶቹ ተማሪዎች ለኮቪድ 19 ወረርሽን ተጋላጭ እንዳይሆኑ አስፈላጊ በመሆናቸው ድርጅቶቹ ላደረጉት ድጋፍ በከተማ አስተዳደሩ እና በተማሪዎች ስም ምስጋና ማቅረባቸውን ከአዲስ አበባ ከተማ ፕሬስ ሴክሬቴሪያት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

