Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአንበጣ ወረርሽኝ ስርጭት አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ በደረሱ ሰብሎች ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል ህብረተሰቡ የመከላከል ዘመቻው አካል እንዲሆን ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአንበጣ ወረርሽኝ ስርጭት አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ በደረሱ ሰብሎች ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል
ህብረተሰቡ የመከላከል ዘመቻው አካል እንዲሆን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በግብርና ሚኒስቴር የአንበጣ ወረርሽኝ መከላከል ቴክኒክ ቡድን ጋር በፅህፈት ቤታቸው ውይይት አድርገዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የአንበጣ ወረርሽኝ ስርጭት ፈጣን እና ሰፊ መሆኑ የመከላከል ሥራውን እጅግ ፈታኝ እንዳደረገው ቴክኒክ ቡድኑ አስታውቋል።
አሁን ካለበት ሁኔታ አንፃር የመከካል ሥራው ኬሚካል በሚረጩ አውሮፕላኖች መታገዝ ስላለበት፤ ከጐረቤት ሀገራት ለአንበጣ ማጥፊያ የሚያገለግሉ አውሮፕላኖችን በድጋፍ ለማግኘት የተለያዩ ጥረቶች በመደረግ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ በበኩላቸው፤ የአንበጣ ወረርሽኝ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ እና ለመከላከል የተጀመሩ ጥረቶችን ማጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል።
የአንበጣ ወረርሽኝ ከጊዜ ወደ ጊዜ በፍጥነት እና በስፋት መጨመሩ በደረሱ ሰብሎች ላይ የሚያደርሰው ጉዳት አሳሳቢ መሆኑን መግለፃቸውን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
መንግስት ችግሩን ለመከላከል የጀመረው ጥረት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን በመጠቆም፤ ህብረተሰቡም የመከላል ዘመቻው አካል እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል፡፡
Exit mobile version