አዲስ አበባ ፣ መስከረም 29፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎና የምክር ቤት አመራሮች የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ቅድመ ዝግጅትን ጎብኝተዋል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስድስተኛው ሃገር አቀፍ ምርጫ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የመከላከያ መንገዶችን በመተግበር እንዲካሄድ ከጤና ሚኒስቴር የቀረበለትን ምክረ ሃሳብ በተጨባጭ በማጤን መወሰኑ ይታወሳል።
በዚህም አጠቃላይ የቁሳቁስ ዝግጅቶችን የተመለከቱ ሲሆን ከዚህ በፊት የነበረውን የድምጽ መስጫ ኮሮጆን ጨምሮ ለ6ኛው ሃገር አቀፍ ምርጫ የተዘጋጁ ሌሎች ዘመናዊ ቁሶችን በማነጻጸር መጎብኘታቸው ታውቋል፡፡
ከጉብኝቱ በኋላ አፈ ጉባኤው አቶ ታገሰ ጫፎ የኢትየጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ2013 ለሚካሄደው 6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ አስፈላጊ የቁሳቁስ ዝግጅት እንዳደረገ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም በቦርዱ በኩል የተደረገው የቁሳቁስ ዝግጅት 90 በመቶ ስለመሟላቱ ማረጋገጣቸውንም ገልፀዋል፡፡
” ምርጫው ተአማኒ፣ ዴሞክራሲያዊና ግልጽ እንዲሆን የሚያስችሉ አስፈላጊ ቁሶች መዘጋጀታቸውንም በጉብኝቱ ወቅት ተመልክተናል” ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብና የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫው ፍትሃዊና ተአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የድርሻቸውን እንዲወጡም አፈ ጉባኤው አቶ ታገሰ ጥሪ አቅርበዋል።

