አዲስ አበባ ፣መስከረም 29፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ማህበራዊ ድረ-ገጽን በአግባቡ አለመጠቀም የህግ ተጠያቂነትን እንደሚያስከትል ተገለጸ፡፡
በንቃተ ህግ ትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ የሰውዘር አበበ እንዳሉት÷ የማህበራዊ ድረ-ገጽ አጠቃቀምን አስመልክቶ በህግ የተቀመጡ ገደቦችን ሳያልፉ ለታለመለት አላማ ብቻ መጠቀም ተገቢ ነው፡፡
ነገር ግን የማህበራዊ ድረ-ገጽን ላልተፈለገ እኩይ ተግባር በማዋል የሀሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግር ለማስተላለፊያነት በመጠቀም የሌሎችን ሰብዓዊ ክብር የሚነኩ እንዲሁም ባልተጨበጠ መረጃ ህብረተሰቡ ግራ እንዲጋባ ለማድረግ ያለአግባብ የሚጠቀሙ አካላትን ተጠያቂ የሚያደርግ የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትና የጥላቻ ንግግርን የሚከለክል አዋጅ ወጥቶ ስራ ላይ እንደዋለም አስታውሰዋል፡፡
በአዋጁ ከተካተቱት መካከልም የጥላቻ ንግግርን በብሮድካስት፣ በህትመት ወይም በማህበራዊ ሚዲያ ወይንም ሌላ ተመሳሳይ ዘዴዎችን በመጠቀም ያስተላለፈ እስከ 2 አመት በሚደርስ እስራትና 100 ሺህ ብር እንደሚያስቀጣ አብራርተዋል፡፡
በተላለፈው የጥላቻ ንግግር ምክንያት በግለሰብ ወይም በቡድን ላይ ጥቃት ደርሶ እንደሆነ የቅጣቱ ጊዜ እስከ 5 ዓመት የሚደርስ ቅጣት ሊተላለፍ ይችላል ብለዋል፡፡
እንዲሁም ሀሰተኛ መረጃዎችን በአደባባይ ስብሰባዎች፣ በብሮድካስት፣ በማህበራዊ ሚዲያ ወይም በሌላ ተመሳሳይ ዘዴዎች አማካኝነት በምስል፣ በጽሁፍ ወይም በቪዲዮ በመጠቀም ያሰራጨ 1 ዓመት በሚደርስ እስራት ወይም የ50 ሺህ ብር ቅጣት ሊተላለፍበት ይችላል ነው ያሉት ዐቃቤ ህጓ፡፡
በተጨማሪም መረጃው ከ5 ሺህ በላይ ተከታይ ባለው ማህበራዊ ድረ-ገጽ የተላለፈና ጉዳት የደረሰ እንደሆነ ግን የቅጣት መጠኑ ከ2 እስከ 5 ዓመት ሊደርስ እንደሚችል መግለፃቸውን ከጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

