አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ትምህርት ሚኒስቴር በመምህርነት ሙያ ሲያገለግሉ የነበሩ ባለሙያዎች ሃገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቀረበ፡፡
ሚኒስቴሩ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ለሰባት ወራት የተቋረጠውን የመማር ማስተማር ሂደት ለማገዝ መምህራኑ በአቅራቢያቸው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ለማገልገል ዝግጅት እንዲያደርጉ ነው ጥሪ ያቀረበው፡፡
የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጌታሁን መኩሪያ “እኔም አስተምራለሁ” በሚል መሪ ቃል ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ከዚህ ቀደም በመምህርነት ሲያገለግሉ የነበሩና በመምህርነት ሙያ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን የመመዝገብ ስራ ይሰራል ብለዋል።
ባለሙያዎቹ በአቅራቢያቸው ባሉ ትምህርት ቤቶች በመሄድ እና በመመዝገብ የትምህርቱን ዘርፍ በሙያቸው እንዲያግዙ ጥሪ መቅረቡን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ትምህርት ሚኒስቴር መደበኛ ትምህርትን በሚያስቀጥልበት ወቅት በትምህርት ቤቶች አካላዊ ርቀትን ለማስጠበቅ የተማሪዎች ቁጥር ከ20 እስከ 25 እንዲሆን መወሰኑን ተከትሎ ትምህርት ቤቶች እንደየ አካባቢያቸው ሁኔታ በፈረቃ ትምህርት እንዲሰጡ መወሰኑ ይታወሳል፡፡

