አዲስ አበባ ፣ መስከረም 30 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ እና ሱዳን ድንበር አካባቢ ያለውን ሠላም ለማረጋገጥ በጋራ እንደሚሠሩ የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ ወታደራዊ ልዑክ ገለጸ፡፡
የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ ወታደራዊ ልዑክ በድንበር አካባቢ ሠላምን ለማረጋገጥ በሚቻልበት አግባብ በባሕር ዳር ከተማ ምክክር እያካሄደ ነው፡፡
የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ፅሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ እርዚቅ ኢሳ አትዮጵያና ሱዳን በባህል፣ በኢኮኖሚ በከፊልም በቋንቋና በሃይማኖት እንደሚቀራረቡ ተናግረዋል፡፡
ሁለቱ ሀገራት ድንበር አካባቢ አልፎ አልፎ የሚስተዋለውን የፀጥታ ችግር ለመከላከል የሚረዳ የተሳካ ውይይት እንደሚያደርጉም ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡
በቅርቡ የሱዳን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የተሳካ ጉብኝት ማድረጋቸው ሀገራቱ ግንኙነታቸውን በኢኮኖሚያዊ ትስስር ለማጠናከር እየሄዱበት ያለውን ርቀት ማሳያ ነው ብለውታል፡፡
የኢትዮጵያ ከፍተኛ ወታደራዊ ልዑክ መሪ ብርጋዴር ጄኔራል ሙሉዓለም ዓድማሱ እና የሱዳኑ ከፍተኛ ወታደራዊ ልዑክ መሪ ሜጀር ጄኔራል ሷልህ አብደላ ኢሳቅ በሁለቱ ሀገራት ድንበር አካባቢ ያለውን ሰላም ለማረጋገጥ በጋራ እንደሚሠሩ አስታውቀዋል፡፡
በቆይታቸውም በሀገራቱ ድንበር አካባቢ አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት የተሳካ ውይይት በማድረግ በትብብር እንደሚሠሩ መግለጻቸውን አብመድ ዘግቧል፡፡

