Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

መንግስት በሳዑዲ ዓረቢያ በሚገኙ ስደተኞች ላይ እየደረሰ ያለው ስቃይ እንዲቆም ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር በትብብር ትሰራለች አለ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ በሚገቡ ስደተኞች ላይ እየደረሰ ያለው ስቃይ እንዲቆም ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር በትብብር መስራቷን እንደምትቀጥል ተገለጸ፡፡
 
የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ መረጃ እንደሚያመለክተው የዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ ያለ ህጋዊ ሰነድ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ በሚገቡና በዚያ በሚኖሩ ስደተኞች ላይ እየደረሰ ባለው ችግር የገባውን ስጋት ኢትዮጵያም ትጋራለች ብሏል።
 
በዚሁ መሰረት በሪያድ እና በጄዳ የሚገኙ የኢፌዲሪ ሚሲዮኖች በሳዑዲ የሚኖሩ ዜጎች ሁኔታ ከምንጊዜውም በላይ በቅርበት እንዲከታተሉ በመደረግ ላይ መሆኑም ነው የገለጸው።
 
መንግስት ያለ ህጋዊ ሰነድ በየመን በማቋረጥ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ የሚገቡትን እንዲሁም በሳዑዲ ዓረቢያ ያለ ህጋዊ ሰነድ የሚኖሩ እና ለችግር የተጋለጡ ኢትዮጵያዊያንን ወደ አገራቸው ለመመለስ ከሳዑዲ አረቢያ መንግስት እና ከሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በቅርበት እየሰራ እንደሆነ ነው የተነገረው።
 
በተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ሰሞኑን እንደተገለጸው ኢትዮጵያ በሳዑዲ እና በመካከለኛው ምስራቅ የሚኖሩና ለችግር የተጋለጡ ዜጎቿን ወደ አገሯ የመመለስ ስራም ተጠናክሮ መቀጠሉም ተጠቅሷል።
 
መንግስት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር በሳዑዲ ዓረቢያ እና በመካከለኛው ምስራቅ የሚኖሩ ለችግር የተጋለጡ ዜጎቻችን ተገቢው ድጋፍ ተደርጎላቸው ወደ አገራቸው እንዲመለሱና ከተመለሱም በኋላ በአግባቡ ወደ መጡበት ማህበረሰብ ተቀላቅለው መደበኛ ኑሯቸውን እንዲመሩ አሁንም አበክሮ ይሰራል ነው የተባለው።
 
እንዲሁም ዜጎች ለህገወጥ አዘዋዋሪዎችና ደላሎች ሰለባ እየሆኑ መቀጠል የለባቸውም በማለት ህገወጥ አዘዋዋሪዎችን ለህግ ከማቅረብ ጀምሮ የዜጎችን ግንዛቤ ለማሳደግ ከፍትኛ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል ተብሏል፡፡
 
ከዚህ ቀደም ከግንቦት 2009 ዓ.ም ጀምሮ ከ400 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን ከሳዑዲ ዓረቢያ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መደረጉንም መረጃዎች ያሳያሉ።
 
በዚህ በተገባደደው ወርም ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር ከ1 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ አገራቸው መግባታቸውንም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።፡፡
Exit mobile version