አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአደሌ-ግራዋ 53 ኪ.ሜ የአስፋልት የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በሆነ ወጪ በይፋ ተጀመረ፡፡
በዛሬው እለት በተካሄደው የመንገዱ ግንባታ ጅማሮ መርሃግብር ላይ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ ከፍተኛ የፌደራል እና የክልል ባለስልጣናት ተገኝተዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በህብረተሰቡ ለዓመታት የቆየ የመንገድ መሰረተ ልማት ጥያቄ ምላሽ ያገኘበትና ፕሮጀክቱ ለክልሉም ሆነ ለሀገር ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው መሆኑን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ በቀለ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ከወሰን ማስከበር ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጉዳዮችን በፍጥነት እየቀረፉ መሄድ ወሳኝ በመሆኑ የሚመለከታችሁ የመስተዳድር አካላትና ነዋሪዎች አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ባለስልጣኑ ኘሮጀክቱ በስኬት እንዲጠናቀቅም የቅርብ ቁጥጥር እና ክትትል እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል፡፡
የመንገድ ግንባታውን የሚያከናውነው ሂቤ ኮንስትራክሽን ግሩፕ በበኩሉ በገባው ቃል መሰረት ፕሮጀክቱን በጥራት አጠናቆ እንደሚያስረክብ ቃል ገብቷል።
መንገዱን ለመገንባት የሚወጣው ሙሉ ወጪ በኢትዮጵያ መንግስት ይሸፈናል።
የአደሌ-ግራዋን 53 ኪሎ ሜትር መንገድ በአሁን ሰዓት በተሸከርካሪ ለመጓዝ ይጠይቅ የነበረውን ከ3 ሰዓታት በላይ የትራንስፖርት ጊዜ ከግማሽ በላይ ያሳጥረዋል።
የአደሌ ግራዋ መንገድ በአካባቢው በስፋት የሚገኘውን ቋሚ የሰብል ምርቶችን ፣ የቁም እንስሳት ውጤቶች ፣ ፍራፍሬና ሌሎችንም ወደ ገበያ አውጥቶ በመሸጥ ነዋሪው ከምርታቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከማድረግ አንጻር ጠቀሜታው የላቀ መሆኑ ነው የተጠቀሰው።
የአደሌ-ግራዋ መንገድ ግንባታ በመስመሩ ተራርቀው ለነበሩ ወረዳዎች እና ቀበሌዎች በቅርበት በማስተሳሰር ይበልጥ በኢኮኖሚ መነቃቃትን ይፈጥርላቸዋል ተብሏል፡፡
እንዲሁም የአካባቢውን ህብረተሰብ የስራ እድል በስፋት እንደሚፈጥር ይጠበቃል፡
ጎጎት ኮንሰልቲንግ ኢንጅነሪንግ የመንገዱን ግንባታ የማማከር እና የመቆጣጣር ስራውን ያካሄዳል ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል አቶ ሽመልስ አብዲሳ በዛሬው ዕለት በበዴሳና በአወዳይ ከተማ የጫት ገበያ ማዕከል አስጀምረዋል፡፡
በአወዳይ ከተማ የሚገነባው የጫት ገበያ ማዕከል በ430 ሚሊየን ብር እንደሚገነባ ተነግሯል፡፡
የፕሮጀክቶቹ ግንባታ በ18 ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡

