Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አዲስ አበባ ለሚገኙ አምባሳደሮችና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ተሰጠ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 2 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አዲስ አበባ ለሚገኙ አምባሳደሮችና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጠ፡፡

የተራዘመው 6ኛ ሃገራዊ ምርጫ፣ ኮቪድ19 እና ኢ ህገ መንግስታዊ የሆነው የትግራይ ክልል ምርጫን የተመለከቱ ጉዳዮች በማብራሪያው ተነስተዋል፡፡

በዚህም 6ኛው ሃገራዊ ምርጫ የተራዘመበትን ምክንያትና ህገ መንግስታዊ አካሄዶችን በተመለከተ ገለጻ ተደርጓል፡፡

በዋናነትም በሃገሪቱ የዴሞክራሲ ግንባታ ትልቅ አሻራ ይኖረዋል የተባለው ሃገራዊ ምርጫ ዝግጅት ከተደረገ በኋላ በኮቪድ 19 ምክንያት መቋረጡ ተነግሯል፡፡

ከዛ በኋላም የትግራይ ክልል ከህገ መንግስቱ ውጭ በሆነ መልኩ ምርጫ ማካሄዱም ተጠቅሷል፡፡ የተካሄደው ምርጫም ኢ ህገ መንግስታዊ እንደሆነና ተቀባይነት እንደሌለው በፌዴሬሽን ምክር ቤት መወሰኑም ተብራርቶላቸዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ የምክር ቤቱን የቀደመ ውሳኔ በመተላለፍ በትግራይ ክልል ን ምርጫ ተከትሎ በክልሉ የተዋቀረው ህግ አውጪ እና አስፈፃሚ አካል ጋር የፌደራሉ መንግስት ግንኙነት ማቆሙን አንስተዋል።

ምክር ቤቱ በቅርቡ ያሳለፈው ውሳኔ ህገወጥ ስራዎችን በህጋዊ መንገድ ለማረም እንጂ ህዝብን ለመጉዳት ያለመ አለመሆኑን የተናገሩት አምባሳደር ዲና፤ የፌደራሉ መንግስት የክልሉን ህዝብ መሰረታዊ የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች ለማሟላት እስከ ታችኛው አስተዳደር ድረስ በቅንጅት እንደሚሰራ አብራርተዋል።

እንዲሁም መንግስት የህግ የበላይነትን እና የህዝብን ጥቅም ለማስከበር ቁርጠኛ አቋም እንዳለውም ነው ቃል አቀባዩ ለዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ያብራሩት።

ከዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ በትግራይ ክልል የተራድኦ ስራዎች በምን መልኩ ይቀጥላል በሚል ለተነሳው ጥያቄ አምባሳደር ዲና በሰጡት ምላሽ፤ ህዝብን በቀጥታ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተራድኦ ስራዎች በክልሉ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር በትብብር ተጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት።

መንግስት ቀጣዩ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲካሄድ የጀመራቸውን የፍትህ እና የዴሞክራሲ ተቋማት ማሻሻያ ስራዎች ይቀጥላልም ተብሏል፡፡

ማብራሪያው ያስፈለገበት ምክንያትም ዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ የተዛባ መረጃ እንዳይዝ ለማድረግ መሆኑንም አምባሳደር ዲና አስረድተዋል፡፡

በለይኩን ዓለም እና በፋሲካው ታደሰ

Exit mobile version