Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በኦሮሚያ ክልል ለ2013 የትምህርት ዘመን ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦሮሚያ ክልል የ2013 የትምህርት ዘመን ለማስጀመር ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋ ገለፁ።

አቶ አዲሱ አረጋ በዛሬው እለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፥ የ2013 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማስጀመር በየደረጃው ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ኮሚቴው የመማር ማስተማር ሂደቱ ትምህርት ሚኒስቴር ኮቪድ19ን ለመከላከል ባስቀመጠው መስፈርት መሰረት እንዲጀመር ለማድረግ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

በክልሉ ተጨማሪ 33 ሺህ የመማሪያ ክፍሎች መገንባታቸውን ያነሱት አቶ አዲሱ፥ ይህም የትምህርት ሚኒስቴር ባስቀመጠው መመሪያ መሰረት የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማከናወን ያስችላልም ብለዋል።

አያይዘውም በክልሉ 11 ነጥብ 2 ሚሊየን ተማሪዎችን ለመመዝገብ እቅድ ተይዞ እስካሁን የእቅዱ 82 በመቶ መከናወኑን ጠቁመዋል።

በአንድ ፈረቃ ከ1 ሺህ በታች ተማሪዎች እንዲማሩ እንደሚደረግና በአንድ የመማሪያ ክፍል ውስጥም 25 እና ከዛ በታች ተማሪዎች ብቻ ይማራሉም ብለዋል፤ አንድ የመማሪያ ዴስክ ለአንድ ተማሪ መሆኑን በመጥቀስ፡፡

በተጨማሪም ለሁሉም ተማሪዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል በነጻ መዘጋጀቱን እና በሁሉም ትምህርት ቤቶች ውሃ የማቅረብ ስራ እንደሚሰራም አስረድተዋል።

እንዲሁም ሁሉም ትምህርት ቤቶች የሙቀት መለኪያ እንዲኖራቸው ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ነው የገለጹት።

በዚሁ መሰረት የ2013 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሂደቱ በሶስት ዙር የሚጀመር ሲሆን በመጀመሪያው ዙር የ8ኛ እና 12 ክፍል ተማሪዎች ጥቅምት 16 ቀን 2013 ዓ.ም ትምህርት ይጀምራሉ ተብሏል፡፡

በ13 ዞኖች ውስጥ በተለዩ ትምህርት ቤቶች ደግሞ ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ፡ም ትምህርት እንደሚጀመርና በአዲስ አበባ ዙሪያ እንዲሁም አዲስ አበባን ከበው በሚገኙ ከተሞች ህዳር 15 ቀን ትምህርት የሚጀምር ይሆናል።

ከመምህራን ጋር ተያይዞ እጥረት ሊያጋጥም ስለሚችል በስራ ላይ ያሉ መምህራን ተጨማሪ ክፍሎችን እንዲያስተምሩ ይደረጋልም ነው የተባለው።

በተጨማሪም በጡረታ ለተገለሉ መምህራን እና የመምህርነት ሙያ ኖሯቸው እስካሁን ስራ ላልጀመሩ ወጣቶችም ጥሪ መደረጉም ተገልጿል።

አቶ አዲሱ በመግለጫቸው አክለውም፥ የነገ ብርሃን የሚል ስያሜ በተሰጠው ፕሮጀክት በ2013 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል 147 ትምህርት ቤቶች የሚገነቡ መሆኑንም አስታውቀዋል።

በዚህ ፕሮጀክት ትምህርት ቤቶቹ በሶስት የተለያዩ አይነቶች የሚገነቡ ሲሆን፥ ከእነዚህ አንዱ የሆነው ልዩ የአዳሪ ትምህርት ቤቶች በነጆ፣ በደሌ፣ አምቦ፣ ነገሌ፣ ቦረና፣ ያቤሎ፣ ሀሮማያ እና ዶዶላ የሚገነቡ ናቸው።

በሁለተኛው 47 ልዩ የነገ ብርሃን ትምህርት ቤቶች የሚገነቡ ሲሆን፥ ቀሪው ደግሞ 100 የ2ኛ ደረጃ እና አዳሪ ትምህርት ቤቶች ናቸው።

ለትምህርት ቤቶቹ ገንባታም 4 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በጀት ተይዟል፡፡

Exit mobile version