አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ ኮሮና ቫይረስ መከላከልን ታሳቢ ያደረገ ትምህርት ለማስጀመር 50 ሚሊየን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ለስርጭት መዘጋጀቱን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
በአፋር ክልል የ2013 ዓ.ም ትምህርት በሚጀመርበት ቅድመ ሁኔታ ላይ የመከረ መድረክ በሰመራ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የትምህርት ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ነቢል መህዲ እንደገለጹት፥ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎቹ የሚሰራጩት በሀገሪቱ በሚገኙ 46 ሺህ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ነው።
ጭምብሎቹ ለተማሪዎች ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል አገልግሎት ላይ የሚውሉ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዲኤታው፥ ለመምህራን የሚታደሉ ተጨማሪ 500 ሺህ ጭምብሎችም እንደሚሰራጩ አመላክተዋል።
ስርጭቱ በዚህ ሳምንት ውስጥ የሚከናወን መሆኑንም ተናግረዋል።
“ለሁሉም ትምህርት ቤቶች ማዳረስ ባይቻልም የሙቀት መለኪያ መሳሪዎችን ለክልሎች ለማሰራጨት ዝግጅት ተደርጓል” ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

