Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በአማራ ክልል የወባ ስርጭት እየጨመረ መምጣቱን ኢንስቲቲዩቱ አስታወቀ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 3 ፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአማራ ክልል የወባ ስርጭት እየጨመረ መምጣቱን የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት አስታወቀ፡፡
በክልሉ በ2012 በጀት ዓመት የወባ ተጠቂዎች ከ2011 በጀት ዓመት የተጠቂዎች ቁጥር በ66 በመቶ ጨምሯል ተብሏል፡፡
በአማራ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የወባ ፕሮግራም አስተባባሪ ማስተዋል ወርቁ እንደገለጹት የክልሉ መልክአ ምድር አቀማመጥ ለወባ መራቢያ ምቹ መሆን፣ የማህበረሰቡ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ መቀነስ እና በአልጋ አጎበር አጠቃቀም ችግሮች ምክንያት ከሳምንት ሳምንት ከፍተኛ የሆነ የወባ ሕሙማን ቁጥር በክልሉ እየተመዘገበ ይገኛል፡፡
ባለፉት ሦስት ወራትም ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች በወባ መያዛቸውን አስተባባሪዋ ተናግረዋል፡፡
በክልሉ 53 ወረዳዎች የኬሚካል ርጭት ለማካሄድ አቅርቦት ያሉት አስተባባሪዋ ይሁን እንጅ በኬሚካል አምራች ፋብሪካው የማምረት ውስንነት ምክንያት መቅረብ የቻለው ከተጠየቀው 75 በመቶ ብቻ ነው፡፡
በዚህም ምክንያት በ22ቱ ወረዳዎች በከፊል የፀረ ተባይ ኬሚካል ርጭት የተካሄደ ሲሆን በዘጠኝ ወረዳዎች ደግሞ ርጭት ማካሄድ አለመቻሉን ገልጸዋል፡፡
በ2013 በጀት ዓመት በክልሉ ለሚገኙ 55 ወረዳዎች 4 ሚሊየን አጎበር ቀድሞ ለማሠራጨት ለጤና ሚኒስቴር ቢጠየቅም ከመተማ፣ ፎገራ እና ገንዳ ውኃ ከተማ አስተዳደር ውጭ በግዥ መጓተት ምክንያት እስካሁን ማሠራጨት አልተቻለም ተብሏል፡፡
ይህ ደግሞ የወባ መከላከል ሥራውን አስቸጋሪ እንደሚያደርገው ተጠቁሟል።
በክልሉ ነፍሰጡር እናቶች እና ከ15 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች ይበልጥ በወባ ተጠቂ መሆናቸውን አብመድ ዘግቧል።
Exit mobile version