Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአፍሪካ ህብረት የሪፎርም አጀንዳ እንዲሳካ ኢትዮጵያ አስፈላጊውን ድጋፍ ታደርጋለች- አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአፍሪካ ህብረት የሪፎርም አጀንዳ እንዲሳካ ኢትዮጵያ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ገለፁ።

37ኛው የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ በቪዲዮ ኮንፈረንስ ዛሬ መጀመሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።

የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤቱ ለሁለት ቀናት በሚያካሂደው ስብሰባ በህብረቱ የ2021 በጀት፣ የህብረቱ ሪፎርም አጀንዳ፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የሽግግር እቅድ እና የፋይናንስ ስትራቴጂ እንዲሁም ሌሎች አጀንዳዎች ላይ በመወያየት ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በስብሰባው ላይ ባደረጉት ንግግር የህብረቱን 2021 መነሻ በጀት በማዘጋጀት ያቀረቡትን የፋይናንስ ሚኒስትሮች እና ቋሚ ተወካይ ኮሚቴዎችን አመስግነዋል።

አሁን የምንገኝበትን የኮቪድ19 ወረርሽኝ እና የአባል ሃገራቱን የኢኮኖሚ አቅም ግምት ውስጥ በማስገባት ኮሚሽኑ በጀት የሚያስፈልጋቸውን ጉዳዮች ቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ መለየት እንዳለበትም ገልጸዋል።

ምንም እንኳ በኮቪድ19 ወረርሽኝ ወቅት የምንገኝ ቢሆንም፣ ቋሚ ኮሚቴው የህብረቱ የሪፎርም አጀንዳ ሂደት እንዲሳካ አመርቂ ስራ ማከናወኑንም ጠቅሰዋል።

ህብረቱ አዲሱን መዋቅራዊ ሪፎርም ተግባራዊ በሚያደርግበት ወቅት የኮሚሽኑን ስራ እና የሰው ሃይሉን ባጣጣመ እና በጥንቃቄ መከናወን እንዳለበትም አሳስበዋል።

መዋቅሩ ወደ ተግባር ሲገባም በሰው ሃይሉ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ በማያሳድር መልኩ መከናወን አለበትም ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ የህብረቱ የሪፎርም አጀንዳ እንዲሳካ አስፈላጊውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥልም አቶ ገዱ በንግግራቸው አንስተዋል።

የህብረቱ የ2021 መሪ ሃሳብ ‘’የምንፈልገውን አፍሪካን ለመገንባት ሥነ-ጥበባት፣ ባህል እና ቅርስ ምሰሶዎች ናቸው’’ እንዲባልም ስምምነት ላይ ተደርሷል።

Exit mobile version