አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 4 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የመማር ማስተማር ሂደቱን በፈረቃ ለማስቀጠል የተያዘው እቅድ እንደየአካባቢው ነባራዊ ሁኔታ የሚወሰን መሆኑን ትምህር ሚኒስቴር አስታውቋል።
የትምህርት ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ገረመው ሁሉቃ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ተቋርጦ የነበረውን የመማር ማስተማር ሂደት ለማስቀጠል በሀገር አቀፍ ደረጃ በርካታ ዝግጅቶች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ተማሪዎችን አካላዊ ርቀታቸውን ጠብቀው እንዲማሩ ለማድረግ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችን መገንባት እና የመማር ማስተማር ሂደቱን እስከ ሶስት ፈረቃ ማድረግ ዋነኞቹ ናቸው ብለዋል፡፡
የመምህር እጥረትን ለመቅረፍም ከዚህ በፊት የማስተማር ልምድ ያላቸው እና አዲስ ተመራቂ ተማሪዎች ሀገራዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ መቅረቡንም አንስተዋል።
ጥሪ የተደረገላቸው መምህራንም በበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚሳተፉ እንጂ ቅጥር የሚፈፅሙ አለመሆናቸውንም ነው ያነሱት፡፡
በበጎ ፍቃዱ አገልግሎቱ የሚሳተፉ የአፕላይድ ሳይንስ ተመራቂዎችም አጭር የማስተማር ክህሎት ስልጠና ወስደው አገልግሎቱን የሚሰጡ ይሆናልም ነው ያሉት።
እነዚህ ተመራቂዎች በመምህርነት ስራ የመቀጠል ፍላጎት ካላቸው በቀጣይ ቅጥር በሚካሄድበት ጊዜ ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው ጠቁመዋል፡፡
መደበኛ አስተማሪዎች ከዚህ ቀደም ከሚያስተምሩት ክፍለ ጊዜ በተጨማሪ አምስት ክፍለ ጊዜ በበጎ ፈቃድ እንዲያስተምሩ የሚደረግ መሆኑን አውስተዋል፡፡
ለዚህም መምህራን ለወራት ተቋርጦ የቆየውን የመማር ማስተማር ሂደት በማስቀጠል ሀገራዊ ሃላፊነታቸው እንደሚወጡ እምነታቸው መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
የመማሪያ ክፍል እጥረትን ለማስወገድ የአርሶ አደር ማሰልጠኛ ጣቢያዎችን፣ የቀበሌ ፅህፈት ቤቶችን እና የሃይማኖት ተቋማት አገልግሎሎት እንዲሰጡ ይደረጋል ብለዋል፡፡
የመማር ማስተማር ሂደቱ በጥሩ ሁኔታ እንዲቀጥል ወላጆችን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
በመላኩ ገድፍ
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

0
People Reached
0
Engagements
Boost Unavailable
Like
Comment
Share

