አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ዝግ ሆኖ የቆየው የአዲስ አበባ ሙዚየም ለጎብኚዎች ክፍት ተደረገ።
ሙዚየሙ ክፍት የተደረገው የአዲስ አበባ ከተማ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ እና ቱሪዝም ኢትዮጵያ በመተባበር ጸረ ተህዋሲያን ርጭት ካካሄዱ በኋላ ነው ተብሏል።
ከዚህ ቀደም በወረርሽኙ ምክንያት ዝግ የነበሩ የቱሪስት መዳረሻዎች ክፍት እየተደረጉ ይገኛሉ።
ከዚህ ቀደምም በአክሱም የሚገኙ ታሪካዊ ሥፍራዎች፣ በሐረር የሚገኙ የግልና የመንግስት ሙዚየሞች፣ ጥያ ትክል ድንጋይ፣ ብሄራዊ ፓርኮች፣ አንድነት ፓርክ፣ በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ ሥፍራዎች ለጎብኚዎች ክፍት መደረጋቸው ይታወሳል፡፡
በዚህ ሳምንት ውስጥም ብሔራዊ ሙዚየም እንደሚከፈት ከቱሪዝም ኢትዮጵያ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

